ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ ክልል ለጥቂት ቀናት የተስተዋለው አንፃራዊ ሰላም ዳግም ወደ ግጭቶች እያመራ መሆኑን ነዋሪዎች ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 25/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የተወሰኑ አከባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በታጠቁ ፋኖ አባላት መካከል ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ከተወሰኑ ቀናት መረጋጋት በኋላ በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች ዳግም መቀስቀሱንና በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ኃላፊዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኝ “ገዎቻ” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከአርብ አንስቶ እስከ ሰኞ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡ ነዋሪው በአካባቢው የሞቱ ሰዎች መሬት ላይ ተዘርረው ማየቱን አክሎ ገልጧል፡፡

የፍኖተሰላም አጠቃላይ ሆስፒታል ኃላፊ ማናየ ጤናው እሁድ እለት የሶስት ሰዎች አስክሬን ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቋል፡፡ ኃላፊው በከተማው ውስጥም ሆነ ከከተማ ውጭ የሚደረጉ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቆሙን ተናግረዋል። “ወደ ባህርዳር የሚወስደው መንገድ ክፍት መደረጉ እንደ ኦክሲጅንና ሌሎች የህክምና አቅርቦትን እንድናገኝ ያስቻለን ቢሆንም ዳግም መንገዱ ዘግተውታል” ብሏል፡፡

ሌላኛው በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ ከእሁድ ጀምሮ በገጠር አካባቢ ያለማቋረጥ ከፍተኛ የተከኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር ገልጧል፡፡ ነዋሪው  የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ከባድ መሳሪያዎችን ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር እና ነዋሪዎችም በፍርሃት ቤታቸውን ለቀው በመውጣት ላይ እንደነበሩ ተናግሯል፡፡

የደብረማርቆስ አጠቃላይ ሆስፒታል ኃላፊ የሆኑት አንዷለም ገረመው ከአርብ ጀምሮ ሆስፒታሉ 29 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን መቀበሉን ጠቅሰው ሶስቱ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸው አልፏል ሲሉ ገልፀዋል። ኃላፊው አያይዘውም መንገዶች በመዘጋታቸው ሆስፒታሉ በህክምና አቅርቦቶችም ሆነ በደም ክምችት እጥረት ውስጥ ይገኛል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ከሐምሌ ወር ወዲህ 183 ሰዎች መገደላቸውን በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወቃል። በኢትዮጵያ በሚገኙ አንዳንድ ክልሎች እያሽቆለቆለ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንዳሳሰበውም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተማሳሳይ መልኩ የአውሮፓ ህብረት በከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት፣ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ እና በርካታ ንፁሃን ሰዎች መገደላቸው እንዳሳሰበው አስታውቆ ወደ ውይይት፣ እርቅ እና ሰላም የሚያመሩ ማንኛውንም ሂደቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button