ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የኢትዮጵያን “ታሪካዊ ጠላቶች” ትንኮሳ ለመከላከል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዝግጁ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅና “የታሪካዊ ጠላቶቿን” ትንኮሳ ለመከላከል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዝግጁ ነው ሲሉ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ማዕከል ለ24ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የአንድነት ኮርስ እጩ መኮንኖችን ማስመረቁን በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ለዓመታት ከራቀችበት የባህር በር ለመመለስ ስራዎችን እያከናወነች ነው ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ መናገራቸውን እና ይህንንም ተከትሎ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶቿ መሰረተ ቢስ ክሶችን እያቀረቡ ነው ማለታቸውን የሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቲቪ ዘግቧል።

ለዚህም የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ልክ እንደሁልጊዜው የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ዝግጁ ነው ብለዋል ያለው ዘገባው ኢትዮጵያ ጠላቶቿን የተከላከለችው በአንድነትና በተባበረ ክንድ በመሆኑ ፈተና በገጠማት ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያ የጦር መኮንኖች የሀገርን ዳር ድንበር በማስከበር ታሪካዊ ገድሎችን መፈፀማቸውንም አብራርተዋል ብሏል።

ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ተቋዳሽ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረችበት ወቅት በመሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ሲሉ ፊልድ ማርሻሉ ተናግረዋል ያለው የመከላከያ ሚኒስቴር መረጃ ሀገራችን ይህን ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት ታሪካዊ ጠላቶቻችን የውስጥ ችግሮቻችንን ለማባባስ የቋመጡበት ጊዜ ነው ሲሉ መግለጻቸውን አስታውቋል።

በመሆኑ የዛሬ ተመራቂዎች የውስጥ የፀጥታ ችግሮችን በማስተካከል ሀገራችን እንደ ስያሜአችሁ አንድ ሆና እንድትቀጥል ሀላፊነት ተጥሎባችኋል ሲሉም ተናግረዋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button