ፖለቲካማህበራዊ ጉዳይዜና ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና ትንታኔ፡ በአማራ ክልል የመሪዎች ለውጥና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ቢደረግም ግጭቶች ተባብሰው ቀጥለዋል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15/ 2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በመንግስት ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂ ሀይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በመቀጠሉ በክልሉ ውጥረት ነግሷል፡፡ የፌዴራል መንግስት የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ ለማደራጀት መወሰኑ፣ ክልሉ አሁን ላለበት አለመረጋጋት፣ የትጥቅ ፍጥጫ እና አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ሆኗል፡፡

በክልል የተስፋፋውን ግጭቶች እና አለመረጋጋቶችን ለመፍታት በወረሃ ሐምሌ የፌዴራሉ መንግስት ስድስት ወር የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ በወቅቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህዝቦችን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ጠቅላይ መምሪያ የሰዓት እላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደቦችን ጨምሮ የተለያዩ ክልከላዎችን ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ላይ መረጋገት ታይቶ ነበር፡፡

በነሀሴ ወር የተባበሩት ምነሰግስታት ድረጅት በአማራ ክልል ከሀምሌ ወር ጀምሮ 183 ሰዎች መሞታቸውን ገልፆ በክልሉ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታዎች እንዳሳሰቡት አስታውቋል፡፡ በመስከረም ወር ዘ ጋርዲያን ከ70 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በፌደራል ወታደሮች መገደላቸውን እና በማጀቴ ከተማ ከአካባቢው ታጣቂዎች ጋር ከፍተኛ ውጊያ ካደረጉ በኋላ ከፍተኛ ዘረፋ መፈጸሙን ዘግቧል።

ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ላሊበላ ከተማ የከባድ መሳሪያዎች ጩኸት ሲሰማ መሰንበቱን ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን ይህ በክልሉ ያለውን ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ማሳይ ነው፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት የተከሰተው በሳምንቱ መጨረሻ በጎንደር ከተማ በፌደራል ወታደሮች እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ ነው።

የጎንደር ከተማ ኮማንድ ፖስት ባወጣው መግለጫ በከተማዋ ከ50 በላይ ሰዎች ሙትና ቁስለኛ መደረጋቸውን አስታውቋል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልገለጉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት ሀይሎች መካከል በተደረገ ውጊያ ንጹሃን ጨምሮ በሁለቱም ተፋላሚዎች ውገኖች በርካታ አባላት መሞታቸውን ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተደጋጋሚ በክልሉ በሚከሰቱ በእንደዚህ ዓይነት ግጭቶች ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ የ19 ዓመቱ አማረ አንዶ ነው። አማረ ነሃሴ 22፣ 2015 በደብረ ታቦር አቅራቢያ ፋርታ ወረዳ በሚገኘው ቤቱ ፊት ለፊት በተካሄደ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ህይወቱን ማለፉን አጎቱ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡

በጋፋት ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው አማረ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዶ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ነበር፡፡

የቤተሰቡ የበኩር ልጅ የነበረው አማረ ይህ አሳዛኝ ከመፈፀሙ ሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን መጨረሱን አጎቱ ገልፀዋል፡፡ “ነሃሴ 22 ጠዋት 1፡ 30 የቤተሰቡ የልብስ ሱቅ ውስጥ እየሰራ ሳለ ከባድ የተኩስ ድምፅ ተሰማ፡፡ ቤታችን የሚገኘው የወረዳው ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ በመሆኑ ካዛ ቀን በፊት የተኩስ ድምፅ ይሰማን ነበር፡፡ ነግር ግን ይህ የተለየ ነበር” ሲሉ የአማረ አጎት ተናግረዋል፡፡

የሚሰማውን ከፍተኛ ድምጽ ለመመልከት ወደ ውጭ የወጣው ቤተሰቡ አስፈሪና አሳዛኝ ትዕይንት ገጠመው። “ አካባቢው ወድሞ፤ አማረ ሰውነቱ ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሎ፣ ህይወቱ አልፎ አገኘነው” ሲሉ አጎቱ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እየተባባሰ የቀጠለው ግጭት አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል። ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርቱ በዜጎች ደህንነት ላይ ስጋት እያስከተለ ያለው አለመረጋጋትና ግጭት በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።

አበበ (ለደህንነቱ ሲባላ ስሙ የተቀየረ) በሸዋ ሮቢት ከተማ ጓደኛው ላይ በመንግስት ሀይሎች የተፈፀመውን አሳዛኝ ግድያ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡  የአይን እማኙ፣ ድርጊቱ እስከተፈፀመበት ቀን ድርስ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በከተማዋ ለሳምንት እንዳልነበሩ ገልፆ ነሳሴ 2 ቀን 2015 የመንግስት ሃይሎች ወደ ሸዋሮቢት ከተማ እንደገቡ የተኩስ ልውውጥ ተካሄዷል ብሏል፡፡

“የመንግስት ኃይሎች ሲደርሱ እኔና ጓደኞቼ ከቤታችን ውጪ ነበርን ” ሲል የተናገረው አበበ “የታጠቁ ሰዎች ወደኛ መጡና የፋኖ አባላት መሆናችንን ጠየቁን” ሲል ገልጧል፡፡ ከእኛ መካከል ማንም የፋኞ አባል የሆነና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት የነበረው ሰው አልነበረም ሲል አክሎ ለአዲስ ስታንዳርድ የተናገረው አበበ ይህንኑ ብንነግራቸውም አንድ ላይ ሰብስበውን ሀብታሙን ጨምሮ ሶስቱን ጓደኞቼን እንዲንበረከኩ አደሯቸው ብሏል፡፡

አበበ ቀጠሎም ሲያስረዳ “ከታጠቁት አንዱ መሳሪያውን ወደ ሀብታሙ ራስ ላይ አነጣጠረ። ሀብታሙ ለህይወቱ በመፍራት ቢለምነውም፣ ያለምንም ማመንታት ተኩሶበት ወዲያው ህይወቱ አለፈ” ብሏል፡፡ አበበ ተጨማሪ ግድያ እንዳይከሰት ያደረገው አዛዡ ግድያውን እንዲያቆሙ የሰጠው ትዕዛዝ ነው ይላል፡፡

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የሰብአዊ መብት ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት አቶ በፍቃዱ ደረባ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ መጠነ ሰፊ ግጭት በማሸጋገሩ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ አደጋ አስከትሏል ብለዋል። በፍቃዱ ጦርነቱ እየተባባሰ በሄደ ቁጥር የሰላማዊ ዜጎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ለህይወትና ንብረት ውድመት ተጋላጭ ይሆናሉ ሲል ገልፀዋል።

በክልሉ ያለውን ቀውስ ለመቅረፍ መንግስት ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣ ምክንያት መሆን አንደሌለበት ያማናሉ። አክለውም መንግስት በአለም አቀፉ ህግ መሰረት የዜጎችን ህይወት የመጠበቅ እና የአብዓዊ መብቶችን መርህን የማክበር ግዴታ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ በክልሉ ከተከሰተው ግጭት እና አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ለእስር ከመዳረጋቸው ቀደም ብሎ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ የግጭት እና የአማፂ ቡድኖች መስፋፋት ገዥው ፓርቲ በሰላማዊ ምንገድ ከመታገል ይልቅ  ግጭትን እንዲመርጥ አድርጎታል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን እንዚህን ጉዳዮች ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ውይይት መሆኑን ያምናሉ፡፡ እሳቸው እና ፓርቲያው አብን፣ የታጠቁ ግለሰቦች ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንዲመጡ በመምከር ከወታደራዊ ሃይል ይልቅ በሃሳብ ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ምህዳርን ለመፍጠር ሲጥሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል። አቶ ክርስቲያን “እነዚህ ሰላማዊ ሙከራዎች ቢኖሩም፣ የገዥው ፓርቲ አባላት በውይይት ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑትን አካላት ወደ ጫካ እንዲመለሱ አስገድደዋቸዋል” ሲሉ ተናግሯል።

የፓርላማ አባሉ “አንድ ሰው በሕዝብ ላይ ጦርነት ሊከፍት አይችልም፤ ግጭት የበለጠ ግጭት ብቻ ነው የሚወለደው” ሲሉ ገልፀው ይልቁንም በአማራ ክልል ያለውን ውጥረት ለመፍታት ውጤታው መሳሪያ ግልጽ ውይይት እና ድርድር መሆኑን አበክረው ገልፀዋል፡፡

እክ እንደ ክርስቲያን ግጭቱን አስቀድሞ በድርድር መከላከል እንደሚቻል የሚያምኑት አቶ በፍቃዱ ሁሉንም ነገር በጦር እፈታለው በሚል ባህል ገዢው ፓርቲም ሆነ ለታጣቂ ቡድኖች ግጭትን እንደ ብቸኛ አማራጭ ማየታቸው፣ ግጭቶች እንዲባባሱ በማድረግ የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን ገልፀዋል።

የግጭት ቀጠና በሆነው አማራ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የክልሉና የፌደራል መንግስት የአመራር ለውጦችን እና ሽግሽጎችን ማደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ አቶ በፍቃዱ ይህ ተግባር ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ያስገኝ እንደሆን እንጂ ችግሮቹን እንደማይፈታ ያምናሉ። ይልቁኑ መንግስት ታጣቂ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆኑትን ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ውይይት እንዲጀምር እና ወሳኝ ማሻሻያዎችን እንዲተገብር ቤፍቃዱ አጥብቆ አሳስበዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button