ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በምዕራብ እና ደቡባዊ ትግራይ የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ አዲስ አስተዳደር እንደሚዋቀር መከላከያ ሚንስትሩ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 16/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃ በላይ (ዶ/ር) የአሸንዳ በአልን አስመልክተው በማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በትግራይ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ከምዕራብ እና ደቡባዊ ትግራይ ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ካምፖች የሚገኙ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና በአከባቢዎቹ አዲስ አስተዳደር ለመመስረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ከሚከበረው የአሸንዳ በአል ጋር በተያያዘ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት የክልሉ ህዝብ በጦርነቱ ሳቢያ ከደረሰበት ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ገና አለማገገሙን፣ ጥያቄዎቹም በሚገባ እንዳልተመለሱለት፣ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እና ንቡር አናኗራቸው አለመመለሳቸውን አስታውቀው ነገር ግን ሁሉንም ጥያቄዎቹን በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ እንዲመለሱለት እየጠየቀ ያለበት ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ካሉ ህገመንግስቱን ማዕከል ባደረገ መልኩ ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቀዳሚነት የተፈናቀለው ህዝባችን ደህንነቱ እና ሰላሙን ባረጋገጠ መንገድ ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ ለማስቻል ሁሉም የሚመለከታቸው የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በተገኙበት የፌደራል መንግስቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ወደ ተግባር ለመለወጥ እየተሰራ ነው ብለዋል። በአጭር ግዜ ውስጥ ህዝቡ ወደ ቀየው ተመልሶ ህገመንግስታዊ መብቱን በሚያረጋግጥ ሁኔታ አስተዳደሩን እንዲያዋቅር ይደረጋል ሲሉ ገልጸው ተፈጥሮ የነበረውን ሁኔታ ተጠቅመው በአከባቢው ተዋቅሮ የነበረው አስተዳደር እንዲፈርስ እንደሚደረግ ትእዛዝ ተላልፎለት የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ሃላፊነቱን ወስዶ እየፈጸመው ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ውጭ ግን በጉልበት እንቅስቃሴ አደርጋለሁ የሚል አካል ካለ የፌደራል መንግስቱ አሁን እያካሄደ ባለው የህግ ማስከበር አካሄድ እንደሚስተናገድ አስታውቀዋል።

የአከባቢዎቹን ሰላም እና ጸጥታ የማስከበሩን ሂደት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት እንደሚያስከብሩ ገልጸው ከመከላከያ አባላት ውጭ ማንም ታጣቂ ሀይል በአከባቢው ምንም አይነት ስልጣን እንደማይኖረው አስታውቀዋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button