ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፕሪቶርያው ስምምነት ሳይሸራረፍ እንዲተገበር፣ የመንግስታቱ ድርጅት መርማሪ ቡድን የስራ ግዜ እንዲራዘም ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15/2016 ዓ.ም፡- የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የፕሪቶርያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር፣ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት የሰየመው የአለም አቀፉ መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ግዜ እንዲራዘም ጠየቀ፤ ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር ሰላማዊ እና በመቻቻል አብሮ መኖር እንዲጎለብት የበኩሉን እንደሚጫወት ገልጿል። በፓርቲው ውስጣዊ ማሻሻሎችን እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ለሳምንት በዘለቀ ስብሰባ በሰላማዊ ትግሉ አካሄድ ዙሪያ፣ በፓርቲው አመራር ውስጣዊ ጉዳዮች፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሮግራሞች ዙሪያ፣ በሰላም ስምምነቱ አተገባበር ዙሪያ እና በፓርቲው ቀጣይ የትግል አቅጣጫ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ማድረጉን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ሳይሸራረፍ እንዲተገበር እና በህገመንግስቱ መሰረት የትግራይ ግዛቶች ተከብረው ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ ጠይቋል፤ በአተገባበሩ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ህወሓት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አመላክቷል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በተጨማሪም በመግለጫው አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገው የሰብአዊ ረድኤት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

የፌደራል መንግስቱ የትግራይ ክልል የደረሰበትን ውድመት የሚመጥን በጀት እንዲመድብ ያሳሰበው መግለጫው በማንነታቸው ምክንያት ብቻ በእስር ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በአፋጣኝ እንዲለቀቁና የተበደሉም ፍትህ እንዲያገኙ ጠይቋል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በተጨማሪም ፓርቲው ያጋጠመውን ውስጣዊና መሰረታዊ የአመራር ድክመት መገምገሙን እና ርዕዮተ አለሙን፣ ፕሮግራሙን በመፈተሽ ሪፎርም ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል።  

ግዜያዊ አስተዳደሩ ያሉበትን ድክመቶች በመፍታት በሁሉም መንገድ እንዲጠናከር ለማድረግ ሁሉም የፓርቲው አባላት ህዝቡን በማሳተፍ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ውሳኔ ማሳለፉንም አመላክቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button