ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ ከ20 በላይ ትልልቅ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2016 .ም፡ በ2015 ዓ.ም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ከ20 በላይ ትልልቅ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደሚገኙ እና ከ630 መዝገቦች በላይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ብሄራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዘገባው አስታውቋል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ አንስቶ እስከ ደቡብ አፍሪካ በተዘረጋ የሰው ንግድ ሰንሰለት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ከ20 በላይ ትልልቅ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመስርቶባቸው ክርክር ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው አሁንም ዋናዎቹን ደላሎች ከመያዝ፣ ግንኙነታቸውን ከመበጣጠስ፣ በመልማዩችና በመዳረሻ ሀገራት ባሉ ተቀባዩች ያለውን ትስስር በማፍረስ በኩል ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ሃላፊው መግለጻቸውን አስታውቋል።

ድርጊቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ክልሎች አባል የሆኑበት ብሄራዊ ምክር ቤት መቋቋሙን የጠቆመው ዘገባው በፌዴራል ደረጃ በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ብሄራዊ የትብብር ጥምረት የፍልሰት አስተዳደር መዘርጋቱንም ኃላፊው መናገራቸውን አካቷል።

የዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት የሚያደርጉት ፍልሰት የሀገር ገጽታ የሚያበላሽ፣ አንገት የሚያስደፋ ከፍተኛ ችግር ያለበት በመሆኑ ብዙ ሥራ መሠራት አለበትም ሲሉ ሃላፊው መናገራቸውን ያስነበበው የፕሬስ ድርጅት ድረገጽ 500 ሺህ ሰዎችን በሕጋዊ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ በመንግሥት የተቀመጠው እቅድ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን በመቀነስ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣልም ማለታቸውን አመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button