ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ወራት ከ120 ሺህ በላይ ዜጎች በህጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር ሥራ እንዲያገኙ ማድረጉን መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2016 ዓ.ም፡- በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ከ120 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እንዲያገኙ ማድረጉን ኢዜአ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልን ዋቢ በማድረግ አስታወቀ።

የውጭ ሀገር ሥራን አማራጭ ለሚያደርጉ ዜጎች መንግስት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሥምምነት በመፈራረም በህጋዊ መንገድ ተሰማርተው የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው መባሉን የጠቆመው ዘገባው ኢትዮጵያ ከሊባኖስ፣ ጆርዳን፣ ኳታርና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር ህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ውል በመዋዋል ዜጎች በህጋዊ መንገድ ሄደው እንዲሰሩ እየተደረገ ይገኛል ማለታቸውን አመላክቷል።

የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት እድል እየተፈጠረ መሆኑን ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል ያለው ዘገባው የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ለሚወስዱ ዜጎች ብቻ ተብለው በተለዩ 94 የሥልጠና ማዕከላት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እየተደረገ ነው ማለታቸውን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የዜጎችን የውጭ ሀገር ሥራ የመሰማራት ፍላጎት በህጋዊ መንገድ ለማሳካት ከተለዩ ሀገራት ጋር በመነጋገርና ሥምምነት በመፈራረም መዳረሻዎችን እያሰፋች ነው ማለታቸውንም አካቷል።

የመዳረሻ ሀገራትን ቁጥር ለማብዛት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እና ኤዥያ ሀገራት የስራ ፍላጎቶች እየመጡ መሆኑንም አስታውቀዋል ብሏል።

የመዳረሻ ሀገራትን ከማስፋት በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አሰራሮችን በማዘመን በወር እስከ 38 ሺህ ዜጎችን መላከ የሚቻለበት አሰራር ተፈጥሯል ማለታቸውንም አስታውቋል።

ከጀርመን የግል ኩባንያዎች ጋር በመነጋገርም የውጭ የሥራ ሥምሪት መስጠታቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button