ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ዩኔስኮ የሸዋል ኢድ በዓል አከባበርን በአለም የማይዳሰሱ ቅርስነት መመዝገቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26/2016 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር የአለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ አድርጎ መመዝገቡን አስታውቋል። ዩኔስኮ በቦትስዋና ከባለፈው ሰኞ ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እያካሄደው ባለው 18ኛው የማይዳሰሱ የአለም ቅርስ ስብሰባው ነው በሀረር የሚከበረውን የሸዋል ኢድ በዓል አከባበርን በአለም ቅርስነት መመዝገቡን ያስታወቀው።

ሸዋል ኢድ በሀረር በጀጎል ዙርያ ካሉ አምስት በሮች በሁለቱ ማለትም በየረር በር እና ፈላና በር በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው።

የሸዋል ኢድ በዓል በማይዳሰስ ቅርስነት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ የተመዘገበ አምስተኛ የኢትዮጵያ ቅርስ ሆኗል።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት በመመዝገቡ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የክለሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።

የሸዋል ኢድ በአል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎም ሀረር በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ ያደርጋታል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገርም ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራን እንድትይዝ ያደርጋታል ብለዋል በመልዕክታቸው።

የክልሉ መንግስትም የአለም ቅርስ የሆነውን ሸዋል ኢድ በአል ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመው ሸዋል ኢድ በዓል የአለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button