ቢዝነስዜና

ቢዝነስ፡  ኦሮሚያ ባንክ 2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1/ 2016 ዓ/ም፡ ኦሮሚያ ባንክ አ.ማ. በ2015 በጀት ዓመት 2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ትርፍ ማግኘቱ ገለጸ። ባንኩ ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው አመታዊ አፈጻጸም ሪፖርት ከተያዘዉ አመታዊ የገቢ ዕቅድ 4% በመብለጥ  8.3 ቢሊዮን ብር አመታዊ ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል። ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ትርፍ በ63% እድገት ማስመዝገቡን በመጥቀስ ዕድገቱም በባንኩ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ባንኩ ገልጿል።

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተም 371 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ያስታወቀው ባንኩ ካለፈው ዓመት የ33% ዕድገት የተመዘገበበት ነው ብሏል። የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ከቀዳሚው ዓመት በ24% በማደግ 54.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል ነው ያለው፡፡ 

የባንካችን አጠቃላይ ሀብት ብር 66 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው ዓመት 27% ዕድገት ማስመዝገቡን ለአዲስ ስታንዳርድ ከተላከው ሪፖርት መረዳት ተችሏል። 

ዓለም-አቀፋዊ ተፅዕኖ በአገራችን ኢኮኖሚ እና የባንክ ዘርፍ ላይ ያሳደረው ቀጥተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች ውስጣዊ የኢኮኖሚ መዛባት እና የሰላም እና የፀጥታ ችግሮችን ተከትለው በተፈጠሩ ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እንድንሻገር አስገድዶናል ያለው ኦሮሚያ ባንክ የመደበኛ ሂሳብ ደንበኞች ቁጥር 4.3 ሚሊዮን ደርሷል በሏል። 

ካለፈው ዓመት በአማካይ የ33% እድገት ማስመዝገቡን የጠቀሰው የባንኩ ሪፖርት አክሎም አጠቃላይ ካፒታል 25% በማደግ 9.1 ቢሊዮን መደረሱን አምላክቷል። 

በመላዉ ሀገሪቱ 503 ቅርንጫፎች ያሉት ባንኩ ተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በድርቅ ለተጎዱ ማህበረሰቦች እርዳታ እና ለሌሎች ማህበራዊ እና ሰብአዊ አገልግሎቶች እና የልማት ጥሪዎችን በመቀበል በአጠቃላይ 73.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button