ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በአማራ ክልል “የየብስ ትራንስፖርትን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር” እየተሠራ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22/2016 .ም፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚገቡ “የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር” እየተሠራ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።

በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ከየብስ ትራንስፖርት አንጻር ችግር ማጋጠሙን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) መናገራቸውን ያስነበበው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የገጠመውን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ እየተሠራ ማለታቸውን አስታውቋል።

በተመሳሳይ ከኢንተርኔት አኳያ ቱሪስት በሚያስተናግዱ ሆቴሎች የኢንተርኔት መስመር የተለቀቀላቸው እንዳሉ ጠቁመው ሁኔታዎች እየተገመገሙ አገልግሎቱ በአጠቃላይ እንዲኖር እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

በተለይ በመጪው የገናና የጥምቀት በዓላት መዳረሻ ድረስ የፀጥታ ኃይሉ ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር ጥምረት በመፍጠር ሠላም እንዲሰፍን፣ ትራንስፖርት እንዳይቆራረጥ፣ እንግዶች እንዳይንገላቱ፣ ከተለያየ አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚገቡ የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር ሰፊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን መግለጻቸውን አካቷል።

“በተጀመረው ሠላም” የየብስ ትራንስፖርት ከተለያየ አቅጣጫ መምጣት ጀምሯል ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል ያለው ዘገባው በቀጣይ ተጠናክሮ ተግባራዊ በሚደረገው የሠላም ሁኔታ የሕዝብ ትራንስፖርት ሙሉ ለሙሉ እንዲጀመር እየተሠራ ነው ማለታቸውንም ጠቁሟል።

በተለይ የገና በዓል መዳረሻ ቀናት ውስጥ ብዙ ነገሮች እንደሚስተካከሉ ጠቁመው፣ እንግዶች በየብስም ሆነ በአየር የትራንስፖርት አማራጮች ወደ ክልሉ መምጣት እንደሚችሉ መግለጻቸውን አስታውቋል።

በአሁን ወቅት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከአዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ጎንደር ላሊባላ እየተሰጠ እንዳለ በመጥቀስ በተጨማሪ ከባሕርዳር ላሊበላና ጎንደር አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button