ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14/2016 ዓ.ም፡- ዳያስፖራው ለሀገሩ አስፈላጊውን ጥቅም እንዲሰጥ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም መመስረቱ ተገለጸ።

ፎረሙ ከ25 ሀገራት በተውጣጡ ከ300 በላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የዳያስፖራ አባላት የተቋቋመ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር) ማሰታወቃቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

የፎረሙ መቋቋም ዳያስፖራው ለሀገሩ ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ በጥናት በመለየት ወደ ተግባር እንዲቀየር ያደርጋል ማለታቸውን ያስነበበው ዘገባው የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረሙ ለፖሊሲ ግብዓት በማቅረብና ዳያስፖራው ሀገሩን ሊጠቅም በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዲሰራ ሰፊ ጥረት እንደሚያደርግ ማመላከታቸውን አካቷል።

ከፍተኛ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ዲፕሎማሲያዊ መድረክ በሳይንስ ሙዚየም ትላንት ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም መካሄዱን እና በመድረኩ በተለያዩ ሀገራት እየሰሩ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት መገኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው መንግሥት ዳያስፖራውን በአሉታዊ መልኩ ሳይሆን ሁለንተናዊ አጋር አድርጎ እንደሚመለከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል ብሏል፡፡

በርካታ ዳያስፖራዎች ለሀገራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም የተወሰኑ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ስለ ኢትዮጵያ ሌትና ቀን አሉታዊ ጉዳዮችን ያሰራጫሉ ሲሉ በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መግለጻቸውን ዘገባው አስታውቋል።

መንግሥት ዳያስፖራውን የሁለንተናዊ አጋር አድርጎ ስለሚመለከት የሁላችንም ሀገር በሆነችው በኢትዮጵያ ጉዳይ በመነጋገርና በመግባባት ለሁለንታዊ ዕድገት አብሮ መስራት ይገባል ማለታቸውንም አካቷል።

አብዛኛው ዳያስፖራ ለሀገሩ በመቆርቆር የፖሊሲ ግብዓት ያቀርባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መንግሥት ስለሰላም ያልተገደበ ድጋፍ በማድረግ ለሀገራቸው ዕድገት አይተኬ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትን አስተያየት በመቀበል አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነው ማለታቸውንም አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button