ዜና

ዜና፡ በትግራይ ክልል በዘንድሮ ትምህርት ዘመን የተመዘገቡ ተማሪዎች 40 በመቶ ብቻ መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24/ 2017 ዓ/ም፡_ በትግራይ ክልል የተማሪዎች ምዝገባ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በዘንድሮ የትምህርት ዘመን የተመዘገቡት ተማሪዎች 40 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸው ገልጿል።

በትግራይ ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ስዩም ሀጎስ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከአንድ ሚሊዮን ያነሱ ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸው ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ለመመዝገብ ብቁ ናቸው ብሏል።

“አጠቃላይ የተማሪዎች ምዝገባ 40 በመቶ ደርሷል ቢባልም በቅርበት ቢታይ የተመዘገቡት ከ20 በመቶ በታች የሚሆኑት ናቸው” ብለዋል፣

በትግራይ ላለው የትምህርት ችግር ቀዳሚው ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ከ106 በላይ ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠለያ ሆነው በማገልገል ላይ በመሆናቸው ነው ተብሏል።

እንደ አቶ ስዩም ገለጻ፣ ይህ ሁኔታ የክልሉ መንግስት ለተወሰኑ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን በክልሉ በሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያካሄድ አስገድዷል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በመሰረተ ልማት እጦት ምክንያት ከገጠሙት ተግዳሮቶች በተጨማሪ ከአቅሙ በላይ የሆነ ትምህርት ቤቶችን የማስተዳደር ችግር ገጥሞታል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከቢሮው አስተዳደር ውጪ ናቸው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ “እነዚህ ትምህርት ቤቶች በአሁኑ ወቅት በአማራ እና በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር” እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አክለውም ጦርነቱ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

“ከጦርነቱ በኋላ 14,000 የሚሆኑ መምህራን ከትምህርት ዘርፍ ውጪ ሆነዋል” ያሉት ዳይሬክተሩ በተጨማሪም በ2012 ዓ.ም. 46,598 የነበረው የትግራይ መምህራን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎ አሁን ላይ ከ32,000 በታች መድረሱን አስረድተዋል።

“ከእነዚህ መምህራን መካከል ብዙዎቹ በጦርነቱ ወቅት ተገድለዋል አልያም በህክምና እና የመሰረታዊ ግብዓቶች አቅርቦት እጦት ምክንያት ሞተዋል ተብሎ ይታመናል” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።

በክልሉ የተካሄደው ጦርነት በትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት አቶ ስዩም፤ ከ2,470 በላይ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው ከ30,000 በላይ ኮምፒውተሮች ተዘርፈዋል ወይም ወድመዋል ብለዋል።

ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችም በትግራይ ክልል ለሚገኙ ህፃናት ትልቅ እንቅፋት መሆናቸው ተገልጿል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ  የሆኑት አቶ ተስፋዬ ገብረመድን በበኩላቸው፤ ክልሉ ከፍተኛ  የሆነ የኢኮኖሚ እጥረት እያጋጠመ እንደሚገኝ ገልጸው ይህም በተማሪዎችም ሆነ በወላጆቻቸው ላይ ተጽዕኖ በማድረስ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

“ጦርነቱ በክልሉ የትምህርት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፣ በርካታ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል።” ያሉት አቶ ተስፋዬ ይህም የሚጠበቀው የተማሪ ምዝገባ መጠን አነስተኛ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።

አቶ ስዩም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ለሚታየው ዝቅተኛ የተማሪዎች ቁጥር እንደ መፈናቀል፣ በጦርነቱ ምክንያት የትምህርት ፍላጎት መቀነስ፣ በቂ የመሠረተ ልማት እና ግብዓቶች አለመሟላት እና በገጠር ያሉ የትምህርት ቤቶች ተደራሽነት ውስንነት ባሉ ምክንያቶች የተከሰተ ነው ባይ ናቸው።

“ጦርነቱ የተማሪዎችን የትምህርት ፍላጎት ሸርሽሯል።” ያሉት አቶ ስዩም አክለውም ብዙዎች ካጋጠማቸው ጉዳት ለማገገም የስነ-ልቦና ድጋፍ ይፈልጋሉ” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በተጨማሪ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና የትምህርት ስርዓቱን ወደነበረበት ለመመለስ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እና የበጎ አድራጎት ተቋማት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

አቶ ስዩም በትግራይ ክልል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ከ22 ወራት በፊት ቢያበቃም ወደ ትምህርት ቤት ያልተመለሱ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

አዲስ ስታንዳርድ በታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም. በትግራይ ለትምህርት ብቁ ከሆኑ ተማሪዎች መካከል ከግማሽ ያነሱቱ ብቻ የትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘታቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

ዘገባው ከሩብ ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች ባለፈው የትምህርት ዘመን በድርቅ እና በቂ የሰብዓዊ ርዳታ ባለመኖሩ ምክንያት ትምህርታቸውን የማቋረጥ ስጋት ላይ መውደቃቸውን አመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button