ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብድር ሸክም ያጎበጣቸው ሀገራት በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በአለም ባንክ አመታዊ ስብሰባ ተስፋ ሰንቀዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28/2016 .ም፡ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የአለም ባንክ በሞሮኮ ማራካቺ ከተማ የሚያካሂዱት አመታዊ ስብሰባ በብድር ሸክም ለሚሰቃዩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት መፍትሔ ይዞ ይመጣ ይሆን የሚል ሀሳብ በመንሸራሸር ላይ ይገኛል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የብድር ሸክም ያጎበጣቸውን ሀገራት መታደግ የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ባስነበበው ዘገባው አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ግብጽ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሊባኖስ፣ ቱኒዝያ፣ ፓኪስታን፣ ስሪላንካ፣ ዩክሬን እና ዛምብያ የሁለቱ የገንዘብ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው የሚመክሩባቸው መሆኑን የዜና አውታሩ ጠቁሟል።

ኢትዮጵያን አስመልክቶ የዜና አውታሩ ባቀረበው አጭር መግለጫ የሀገሪቱ የብድር እዳ የተከማቸው በዋነኝነት የኮቪድ ወረርሽ ያሳረፈው የኢኮኖሚ ጫና እና በትግራይ የተካሄደው እና ለሁለት አመታት የዘለቀው ጦርነት መሆኑን አስታውቆ የአሜሪካ መንግስት በሀገሪቱ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ  ከቀረጽ ነጻ መብቶችን በማንሳቱ መሆኑን ገልጿል።

ከሁለት አመታት በፊት ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የብድር ማስተካከያ እርምጃዎች እንዲደረግላት ኢትዮጵያ ለቡድን ሃያ ሀገራት አመልክታ እንደነበር የዜና አውታሩ በዘገባው አውስቷል። በተመሳሳይ ባሳለፍነው አመት 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቻይና የኢትዮጵያን የበድር እዳ ክፍያ በከፊል እንዲዘገይ መፍቀዷን ጠቅሷል።

አለም አቀፉ የሀገራት የመበደር አቅምን ደረጃ የሚሰጠው ተቋም ሙዲስ ባሳለፍነው አመት ነሃሴ ወር የኢትዮጵያ ብድር የመመለስ አቅም ደረጃ ከነጌቲቭ አውጥቶ ማስቀመጡን እና ይህም ሀገሪቱ ያቀረበችው የብድር መክፍያ ማስተካከያ ተቀባይነት አግኝቶ ማስተካከያው ይደረጋል ከሚል ተስፋ እና ኢኮኖሚዋ በፍጥነት ወደ ማገገም ይሄዳል ከሚል የመነጨ መሆኑን የዜና አውታሩ በዘገባው አመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button