አዲስ አበባ፣ ያካቲት 7/ 2016 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል መራዊ ከተማ “ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ ርምጃ በጸጥታ ኃይሎች አልተፈጸመም” ሲል አስተባበለ።
መንግስታዊው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት 5 ቀን 2016 ባወጣው ሪፖርት በሰሜን ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. “ከ45 በላይ ሲቪል ሰዎች በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ ተገድለዋል” ሲል አስታውቋል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው፣ ሰዎቹ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎቹ ከሕግ ውጭ የተገደሉት “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት ነው። በተጨማሪም “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ማረጋገጡን ኮሚሽኑ አክሎ ገልጿል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በተጠቀሰው ዕለት በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ግጭት እንደነበር አርጋግጠው “ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ ርምጃ በመንግሥት ኃይሎች አልተፈጸመም” ሲሉ ውንጀላውን አስተባብለዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊቱ ርምጃ የወሰደው፣ “ጥቃት በፈጸሙበት ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ታጣቂዎቹ “በተለያዩ አቅጣጫዎች መከላከያ ሠራዊቱ የሰፈረበትን ካምፕ በማፈን መሣሪያ እና ሎጂስቲኩን ለመዝረፍ በመንቀሳቀሳቸው ራሱን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ ነው እርምጃ የወሰደው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ዶክተር ለገሰ፣ መከላከያ ሠራዊት ”ራሱን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ እርምጃ ሲወስድ እነዚህ ኃይሎች ተመልሰው ወደ ግለሰቦች ቤት ነው የገቡት” በማለት ገልጸው “ወደ ግለሰቦች ቤት በሚገቡበት ጊዜ በሕጉ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት አሰሳ ሲያደርግ መልሰው ተኩስ ከፈቱበት” ሲሉ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቱ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ፣ ወይበይኝ ቀበሌ ለወታደራዊ ቅኝት የተሰማሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ 6 ሲቪል ሰዎችን ከየቤታቸው አውጥተው ከሕግ ውጭ እንደገደሏቸው የገለጸውን በተመለከተ ሚኒስትሩ “እንደዚያ አይነት እርምጃ ስለመወሰዱ ተረጋግጦ የመጣ መረጃ የለም” ብለዋል።
አክለውም “ሲቪል ይቅርና ታጣቂ እንኳን ለማጥቃት ሄዶ እጅ እስከሰጠ ድረስ የሚገደልበት ሥርዓት የለም። ሊሆንም አይችልም” ብለዋል። “እንዲህ ሆኖ ከሆነም ራሱ መከላከያ ተቋሙ እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የተፈጸመው ግድያ በርካታ ሀገራትና ተቋማት እያወገዙ ይገኛሉ። ትላንት የካቲት 6 ቀን ዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያ በሚገኘው አምባሲዋ በኩል ንጹሃን ዜጎች ኢላማ መደረግ እንደሌለባቸው በመግለጽ በመራዊ የተፈጸመውን ግድያ “ሙሉ ምርመራ” እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች።
በተጨማሪም ዩናይትድ ኪንግደም ዓመፅ እንዲቆም እና በግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ውይይት ለማድረግ ጥረቶችን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርባለች።
ሌላኛው በመራዊ በተፈጸመው ግድያ “እጅግ እንደሚያሳስበው” የገለጸው በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ነው። አምባሲው ለንጹሃን ጥበቃ ማድረግ መሰረታዊ የሰብዓዊ ህግ አካል መሆኑን ገልጾ ግጭትን ለማቆም ውይይት ብቸኛው መንገድ መሆኑን አመላክቷል።
የአውሮፓ ኅብረት ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ በመራዊ ከተማ በተፈጸመው የሲቪል ሰዎች ግድያ ላይ “ገለልተኛ ምርመራ” እንዲካሄድም ጥሪ አቅርቧል። የአሜሪካ መንግሥትም ኢትዮጵያ በሚገኙት አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ በኩል “ገለልተኛ ምርመራ” በማድረግ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አስተላልፏል።
ነገር ግን ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በጉዳዩ ላይ ምርመራ የሚያደርግ “ሌላ አካል” እንደማይኖር እና ጉዳዩ የሚመለከተው በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ እንደሆነ ተናግረዋል። አክለውም “ጥሪውን ያቀረቡት የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ መንግሥት “ስለ ኢትዮጵያ ሁሌ እንዳሳሰባቸው ነው። ነገር ግን ይኸ ነው የሚባል የሚደረግ ነገር የለም” ብለዋል።
“የራሳችን ተቋሞች አሉ። ተቋሞቻችን ለሕዝብ ተጠያቂ ናቸው” ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ “የትኛውም አካል ጥፋት ካጠፋ፤ የትኛውም አካል ጉዳት ካደረሰ ሕጉ እና አሠራሩ በሚፈቅደው መሠረት እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ተናግረዋል።
አሳሳቢነቱ በቀጠለው በአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ምክንያት ባሳለፍነው ጥር ወር ብቻ በመራዊ የተፈጸመውን የሲቪል ሰዎች ግድያ ጨመሮ ከ 66 በላይ ሲቪል ሰዎች “በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ” መገደላቸውን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርቱ መረዳት ተችሏል። አስ