ዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ ክልል በጥር ወር ብቻ ቢያንስ ከ66 በላይ ሲቪል ሰዎች በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ያካቲት 5/ 2016 ዓ/ም፦ አሳሳቢነቱ በቀጠለው በአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ምክንያት ባሳለፍነው ጥር ወር ብቻ ከ 66 በላይ ሲቪል ሰዎች “በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ” መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ኮሚሽኑ ይህን ያለው በአማራ ክልል አሳሳቢነቱ የቀጠለው የትጥቅ ግጭት እና በሲቪል ሰዎች ላይ ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎችን በተመለከተ ዛሬ ያካቲት 5፣ 2016 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ ነው። 

ኮሚሽኑ በሰሜን ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ኃይሎች (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚጠሩት) መካከል ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ፣ ማንነታቸው ማረጋገጥ የተቻለ ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ብሏል። 

ሰዎቹ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎቹ ከሕግ ውጭ የተገደሉት “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት መሆኑን ኢሰመኮ አስታውቋል። 

በተጨማሪም “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ማረጋገጡን ኮሚሽኑ አክሎ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ከደረሱት በርካታ ጥቆማዎችና ከልዩ ልዩ መረጃ ምንጮች ከተሰበሰቡት የሲቪል ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ እስከአሁን ድረስ ማንነታቸውን በመለየት ለማረጋገጥ የተቻለው 45 ሲቪል ሰዎችን ብቻ ሲሆን፤ ነገር ግን የጉዳቱ መጠን ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል “ምክንያታዊ ግምት” ለመውሰድ ተችሏል ብሏል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከህግ ውጭ ከተገደሉት መካከል ለቀን ሥራ በጠዋት ከቤታቸው ወጥተው ድንገት ተኩስ ሲከፈት በአንድ ቦታ ተጠልለው የነበሩ 18 ሲቪል ሰዎች የተገደሉ መሆኑን ምስክሮች ገልጸዋል ያለው መግለጫው ቀበሌ 02 አካባቢ በተለምዶ ሚሊኒየም ተብሎ በሚጠራ ሰፈር አንድ የጠፋ አባልን ሲያፈላልጉ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “በፍለጋው አልተባበሩም” ያሏቸውን 8 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን እንዲሁም 12 ባጃጆች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መቃጠላቸውን ገልጸዋል ሲል አክሏል፡፡

በሌላ በኩል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የዕድውኃ ከተማ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው ከወጡ በኋላ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ፣ እንዲሁም መንገድ ላይ የተገኙ ቢያንስ 15 ሰዎች (ሴቶችን ጨምሮ) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ  መገደላቸውና በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ አመላክቷል። 

በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ፣ ወይበይኝ ቀበሌ፣ አብሥራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለወታደራዊ ቅኝት በአካባቢው የተሰማሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ 6 ሲቪል ሰዎችን ከየቤታቸው አውጥተው ከሕግ ውጭ እንደገደሏቸው ምስክሮች ለኢሰመኮ አስረድተዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በዚህ ግጭት በሁሉም ወገኖች በተለይም በየአካባቢው ነዋሪዎችና በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ሥቃይ እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ወገኖች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ሰላማዊ ውይይት መሆኑን ተቀብለው በቁርጠኝነት ይተገብሩት ዘንድ፣ እንዲሁም የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና የተበደሉም እንዲካሱ አሁንም በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button