ዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ግብረ ሰዶማዊነትንና ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራት “አስርጎ በማስገባት ስምምነቶች እንዲፈጸሙ” ለማድረግ ያለው ሃደት በአፋጣኝ እንዲፈተሽ ሲኖዶሱ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5/ 2016 ዓ/ም፦ ግብረ ሰዶማዊነትንና ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራት የንግድ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የፍትሕና የሰብዓዊነት ግንኙነቶች አካል በማድረግ በቃላትና በዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አስርጎ በማስገባት አሣሪ ስምምነቶች እንዲፈጸሙ ለማድረግ ያለው ሃደት በአፋጣኝ እንዲፈተሽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ጠየቀ።

የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና ግብረ ሰዶማዊነትን አስመልከቶ እየተደረጉ ያሉ ሁለገብ ተጽእኖዎችንና መመሪያ የማስለወጥ ማግባባቶችን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው  ቋሚ ሲኖዶሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ብሎም የአፍሪካ መንግሥታት የአህጉሪቷን ሃይማኖታዊ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ዕሴቶች አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ቋሚ ሲኖዶስ ጥብቅ የሆነ የአደራ ጥሪውን ያስተላልፋል ብሏል፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ ይህን ያለው፤ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በአውሮፓ ኅብረት እና በአፍሪካ፣ በካሪቢያንና በፓስፊክ ሀገራት መካከ የተፈረመውን የሳሞአ ስምምነት ኢትዮጵያ መፈረሟን የሚቃወሙ ዘመቻዎች መካሄዳቸውን ተከትሎ ነው። ስምምነቱ “ግብርሰዶማዊነት በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚያደርግ ነጥቦችን ያካተተ ነው” በሚል በርካቶች ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድታቋርጥ እየተጠየቁ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶ፤ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫና በማሳደር የአፍሪካና የምሥራቁ ዓለም ሀገራት ግብረ ሰዶማዊነትንና ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራት እንዲቀበሉ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉትን “ድብቅና ግልጽ እንቅስቃሴዎችን” በጽኑ እንደሚቃወም አስታወቋል፡፡

“ይህ ግብረ ርኩሰት በዘመናችን ተቀባይነት እንዲኖረው፣ የሚደረጉ ሁለገብ ማግባባቶች፣ ተጽዕኖዎችና ተያያዥነት ያላቸው ስምምነቶች በሀገራችን መንግሥት ተቀባይነት አግኝተው እንዳይፈጸሙ ቋሚ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል” ብሏል።

ሲኖዶሱ “በስምምነቱ ሰነድ ጤናማ መስለው የሠረፁ ዐረፍተ ነገሮች ውስጥ እንደታየው በጾታና ሥርዓተ ጾታ መብት፣ የሥርዓተ ጾታ ትምህርት ጋር በማያያዝ ጾታን በቀዶ ጥገና የመቀየር ውርጃ፣ ልቅ የሆነ የተመሳሳይና ተቃራኒ ጾታ ግንኙነትን መፍቀድ፣ ግለሰቦችን እና ማኅበረሰብን መረን በማድረግ ውስብስብ ለሆኑ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ችግሮች የሚዳርጉ መሆናቸውን እንደሚያምን” ጠቅሷል።  

ግብረ ሰዶማዊነት በማንኛውም የቃላት አግባብ ተገልጦ በጾታ መብት መካተት የማይችል ነው ያለው ቋሚ ሲኖዶሱ ይህን አስመልክተው የሚደረጉ ስምምነቶች የሀገራችንን ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ዕሴት የሚጥሱ መሆኑ ታውቆ ሁሉም ዜጎች እንዲቃወሙት፣ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለው በጥብቅ አሳስቧል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሲኖዶሱ አክሎም ግልጽ የሆኑ ግብረ ሰዶማዊነትን የሚያበረታቱ፣ የሚያዛምቱ፣ ድብቅና እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉ አካላት በተመለከተ ከድርጊቸው እንዲቆጠቡ፣ በንሥሓ እንዲመለሱ ቅድስት ቤተክርስቲያን በጥብቅ ታሳስባለች ሲል በመግለጫው ገልጿል።

በመጫረሻም የሥርዓተ ትምህርት መማሪያ ሲዘጋጅ፣ ሀገር በቀል ደንቦችና መመሪያዎች ሲወጡ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ስምምነቶች ሲፈጸሙ በሀገሪቱ ያሉ የእምነትና የባህል፣ ዕሴቶችን፣ የሕግ ማዕቀፎችንና የሥነ ምግባር መርሆችን ተጠብቀው እንዲፈጸሙ ጥሪውን አቅርቧል።

በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ የፈጸመችውን ስምምነት በጽኑ አውግዟል። ጉባኤው ህዳር ወር 5 ቀን 2016 ዓ/ም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑ የአፍሪካ የካሪቢያንና የፓሲፊክ ሀገራት ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ጸንቶ የሚቆይ የንግድና ኢኮኖሚ አሳሪ የአጋርነት ስምምነትን ከአውሮፓ ኅብረት መፈረሙን ገልጿል።

የስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮችና ነጥቦች ሲፈተሹ ከየሃይማኖታችን ሕግጋትና አስተምህሮ ጋር በእጅጉ የሚቃረኑ ሀሳቦችና አቅጣጫዎች የያዘ ሰነድ ነው ብሏል። በዚህም መሰረት ስምምነቱ በአህጉሪቱ ለሚገኙ ልጆችና ታዳጊዎች ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርት (Comprehensive Sexuality Education) የተባለ እጅግ አደገኛ ኢግብረገባዊና ልቅ የወሲብ ትምህርት እንዲማሩ የሚያስገድድ ነው በሏል።

በተጨማሪም በሰነዱ በበርካታ ሥፍራዎች የተጠቀሰው “Gender” (ጾታ) የሚለው ቃል ወንድና ሴት ተብሎ እንደሚተረጎም በስምምነቱ በግልጽ ባለመቀመጡ ይልቁንም በርካታ ጾታዎች እንዳሉ በማስመሰል ሀገራትን የሚያደናግሩባቸው እንደ (sexual orientation አና gender identity)ን የመሳስሉ ግብረሰዶማዊ አስተሳሰቦችን የያዙ ዶክመንቶች በስም ተጠቅሰው በስምምነቱ ውስጥ ተካተዋል ተብሏል። ስምምነቱ የወላጆችን መብት የሚጥስና የኢትዮጵያዊ ቤተሰብ እሴቶችን አደጋ ላይ የሚጥሉ አንቀፆችን የያዘ ስለመሆኑ ጉባኤው አረጋግጫለው ሲል ገልጿል።

በመሆኑም ጉባኤው መንግስት የአዲሱን የሳሞአ የንግድና የኢኮኖሚ የአጋርነት ስምምነትን በርካታ ጎጂ ጎኖች እንዳሉት በማመን ከዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ ራሷን እንድታገልል በማድረግ መንግስታዊ ኃላፊነቱንና አደራውን በተግባር እንዲወጣ በአጽንኦት ጠይቋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button