ዜና

ዕለታዊ ዜና፡ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚቃጣ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ኢዜማ ጠየቀ 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6/ 2016 ዓ/ም፡_ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚቃጣ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም እና መንግስት ግድያ የፈጸሙ የጸጥታ አካላት ላይ የፍትህ እርምጃ እንዲወስድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጠየቀ። 

ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፓርቲው በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስን ጥቃት ፍጹም የሚያወግዝ እና በአስቸኳይ ሊቆም የሚገባ መሆኑን ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባሉት ግጭቶች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡ መገንዘብ ችለናል ያለው ኢዜማ በቅርብ ጊዜ በሰሜን ጎጃም ዞን በመርአዊ ፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረታ እንዲሁም ምዕራብ ጎጃም ቋሪት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ለዚሁ ማሳያ ናቸው ብሏል።

መንግሥት “ይህንን ዓይነት ጸያፍ ተግባር የፈጸሙ የጸጥታ አካላትን” ለይቶ አስፈላጊውን የፍትህ እርምጃ ወስዶ ውጤቱን ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ ኢዜማ ጠይቋል።

በተጨማሪም በክልሉ መንግሥት እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት “እየተሳተፉችሁ ያላችሁ አካላት ለሰላማዊ ንግግር በራችሁን ክፍት በማድረግ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ማኅበረሰቡ እየደረሰበት ካለው ቀውስ እንድትታደጉት” ሲል ጥሪ አቅርቧል።  

በማያባራ ግጭት ማህበረሰቡን ለባሰ መከራና እንግልት ከመዳረግ ያለፈ ይህ ነው የሚባል ዘላቂ መፍትሔ አይገኝም ያለው ድርጅቱ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ትክክለኛውና አዋጩ መንገድ በውይይት፣ በንግግር እና በድርድር በማመን በቁርጠኝነት በመሥራት ብቻ እንደሆነ አሁንም ደግመን ለማስታወስ አንወዳለን ብሏል፡፡አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button