ዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በትግራይ 105 ትምህርት ቤቶች ተፈናቃዮች ተጠልለውባቸዋል፣ 522 የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ ሀይሎች ስር ናቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5/2016 ዓ.ም፡- በዶ/ር ዲማ ነጎ የተመራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በትግራይ ክልል ተከስቶ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ በማስመልከት የመስክ ምልከታ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተጠቆመ።

በመስክ ምልከታውም በክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የቀረበውን ገለፃና ሪፖርት አዳምጧል።

ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ካቀረቡት መካከል የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሲሆን በትግራይ ክልል ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 105 የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ተፈናቃዮች እንደተጠለሉባቸውና 522 የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ ሀይሎች ሥር እንደሚገኙ አስታውቋል። ይህም ልጆች ትምህርት እንዳይማሩ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ጠቁሟል።

የተፈጥሮ ድርቅ ለክልሉ ስጋት ሁኗል፣ 36 ወረዳዎች በድርቅ ተጎድተዋል፣ በተለያዩ የክልሉ ቀበሌዎች ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ህዝብ ተጎድቷል ሲሉ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ፍስሃ ባራኪ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በክልሉ መዘራት ከነበረበት 1.3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 49 በመቶ ብቻ እንደታረሰ አቶ ፍስሃ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተው ያለው መረጃው በጦርነቱ ምክንያት 335 የጤና ተቋማት እንደወደሙና ማህበረሰቡም ወባ፣ ታይፈስ፣ ራቢስና ሌሎች በሽታዎች እየተባባሱ በመምጣታቸው እና በምግብ እጥረት ምክንያት በሽታዎችን መቋቋም አልቻለም ማለታቸውን አመላክቷል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጎዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነጎ ችግሩ በጣም ውስብስብ እንደሆነና የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የተለያዩ አካላት ሊሳተፉበት እንደሚገባ አስረድተዋል ያለው የምክር ቤቱ መረጃ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ማንኛውም ማህበረሰብ ምግብ አጥቶ መሞት የለበትም ማለታቸውንም አስታውቋል።

ቋሚ ኮሚቴው አያይዞም የተጎዳውን ማህበረሰብ ለማገዝ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ረገድ ድምፅ እንደሚሆንና ማህበረሰቡ በስነ ልቦና እንዳይጎዳ ችግሮች በርብርብ እንዲፈቱ የሚዲያ ሽፋን ሊሰጣቸው ይገባል ማለቱንም መረጃው አካቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button