ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ ኢሰመኮ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዙሪያ ያወጣሁት ሪፖርት ትግራይን አላካተተም፣ ሪፖርቱ በተሳሳተ አረዳዳድ ተሰራጭቷል ሲል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/2016 .ም፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አስመልክቶ ባወጣው ሁለተኛው ሪፖርት በትግራይ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ወቅት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ መኖሪያቸው እየተመለሱ ነው በሚል ያወጣሁት ሪፖርት የአማራ እና አፋር ክልልን እንጂ የትግራይ ክልልን ተፈናቃዮች አያካትትም ሲል ዛሬ ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋዊ ፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ አስታውቋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. የኮሚሽኑን 2ኛ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶችን ሁኔታ በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ በተሳሳተ አረዳድ ተመርኩዞ ነው ሲል ወቅሷል።

የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ የኮሚሽኑ ሪፖርት በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በብዛት ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እንደተመለሱ እና ሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው ስሕተት ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል ማለቱን ጠቁሟል።

ሪፖርቱ ይህንን መሰል መረጃ እንደማያካትት፣ የሪፖርቱ አካባቢያዊ ወሰን የትግራይ ክልልን እንደማይጨምር በሪፖርቱ የተገለጸ መሆኑን ያመላከተው መግለጫው በተሳሳተ አረዳድ ስለተሰራጨው የተሳሳተ መረጃና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር መነጋገሩን አስታውቋል።

በዚህም አመታዊ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ እና በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ክልሎች የሚሸፍን መሆኑን ማስረዳቱን እንዳብራራ ጠቁሟል።

ስለሆነም የትግራይ ክልል በሪፖርቱ የተሸፈነ አለመሆኑን በድጋሚ ለማስረዳትና ለማሳወቅ ተችሏል ያለው የኢሰመኮ መግለጫ የትግራይ ክልል በዚህ የጊዜ ወሰን ሊካተትበት ያልቻለበት ምክንያት ሪፖርቱ በተጠናቀረበት ወቅት ክልሉ በጦርነት ሳቢያ ተደራሽ ስላልነበር መሆኑን ገልጿል።

በሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ፣ በተለይም በወቅታዊው አስቸጋሪ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዐውድ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ነባራዊ ሁኔታ ይህን መሰል የተሳሳቱ አረዳዶች፣ እንዲሁም ሆን ተብለው የሚሰራጩም የተሳሳተ መረጃዎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም ኮሚሽኑ በተቻለ ዐቅም እና የጸጥታ ሁኔታው በፈቀደ ጊዜ ሁሉ ተደራሽ በሆነ መልኩ የሚያደርገውን የምርመራ እና ክትትል ሥራ የሚቀጥል ነው” ሲሉ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ መናገራቸውን መረጃው አካቷ።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚሸፍን ሌላ የክትትል ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተም ኢሰመኮ ሲያከናውን የቆየው ክትትል ሪፖርት ላይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ምላሽ የተገኘ መሆኑን እና ተገቢው ሂደት እንደተጠናቀቀ ሪፖርቱ የሚቀርብ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አስመልክቶ ባወጣው ሁለት ሪፖርቶች በትግራይ ክልል ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው እየተመለሱ ነው ሲል ያወጣው ሪፖርት ፍጹም ሐሰት ነው ሲል የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ መኮነኑን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button