ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ላይ ያተኮረ የዲፕሎማሲ አውደ ርዕይ በቀጣይ ሳምንት ይጀመራል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25/2016 .ም፡ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ እና በወቅታዊ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ላይ ያተኮረ የዲፕሎማሲ አውደ ርዕይ በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት ከጥር 02 ቀን እስከ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የአውደ ርዕዩ ዓላማ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ታሪክ በማሳየት ኢትዮጵያ በአፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች የተጫወተቻቸውን ሚና ማሳየት አንዱ መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል ያለው መረጃው ወቅታዊውን የሀገሪቱን የባለብዙ ወገንና ሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስኬትና ተግዳሮቱን ማሳየት፣ በዚህም ህብረተሰቡ ደጋፊ እንዲሆን ማስቻልም ሌላው ዓላማው ነው ማለታቸውንም አካቷል።

በዲፕሎማሲ ሳምንቱ ላይ አሁን ካለንበት የዲጂታል ዘመን አንፃር የአዲሱ ዘመን ዲፕሎማሲን በመጠቀም ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ ወረት በመጠቀም የበለጠ ተደማጭ ለመሆን እያደረገችው ያለውን እንቅስቃሴ ማመላከትም የአውደ ርዕዩ ዓላማ መሆኑን አምባሳደር ዶ/ር መለስ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የአገሪቱን የዲፕሎማሲ ታሪክ እንዲያውቅና አቅም እንዲረዳ፤ ድጋፍ እንዲያደርግ እና አመኔታው እንዲገነባ፤ በመጪው ዘመኑም አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማነሳሳትም ሌላው የአውደ ርዕዩ ዓላማ ነው መባሉን መረጃው አመላክቷል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ዘመናት ተሻጋሪ ስራ የሚዘክረው አውደ ርዕይ የተቋሙን ትውስታ ሰንዶ ለመያዝም ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ቃል አቀባዩ በዝግጅቱ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ ተቋም ከተመሠረተ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የሰነደ መጽሐፍ እና የዲፕሎማሲ ጆርናል ይፋ ይሆናል ማለታቸውን አስታውቋል።

ስድስት ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት የፓናል ውይይት እና የነገ ዲፕሎማቶችን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ የተማሪዎች ጥያቄ እና መልስ ውድድርም ይካሄዳል ተብሏል። በዚህ ሁነት ኢትዮጵያ ከመንግሥታቱ ማኀበር እስከ ብሪክስ አባልነት የተጓዘችበትን የዲፕሎማሲ መንገድ ያሳያል ያለው ዘገባው የዲፕሎማሲ ሳምንቱ “ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ” በሚል መሪ ሐሳብ በሳይንስ ሙዚየም ውስጥ እንደሚካሄድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button