ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ሶስት የትግራይ ፓርቲዎች ለማካሄድ ያቀዱትን ሰልፍ የመቐለ ከተማ አስተዳደር መከልከሉ “ተገቢ ባለመሆኑ” ሰልፉ በታቀደው ቀን ይካሄዳል ሲሉ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27/ 2015 ዓ.ም፡- ሶስት የትግራይ ፓርቲዎች ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ብሄራዊ ባይቶ ዓባይ (ባይቶና) እና ውድብ ናፅነት ትግራይ በተከታታይ ከጳጉሜ 2 አስከ 4 /2015 ዓ.ም በመቐለ ከተማ የአደባባይ የተቋወሞ ስልፍ ለማካሄድ ያስተላለፉን ጥሪ የከተማ አስተዳደር መከልከሉ ተገቢ ባለመሆኑ ሰላማዊና ለውጥ ፈላጊውን ህዝባችን ይዘን በያዝነው የግዜ ሰሌዳ ሰልፉን እናካሄዳለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የፓለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ነሃሴ 23 /2015 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ” መሰረታዊ ለውጥ ” በሚል መሪ ቃል በመቀለ ከተማ ሁሉም የህብረተሰበረ ክፍል የሚሳተፍበት የተቋውሞ ሰልፍ ጠርተዋል። ከጳጉሜ 2- 4 ለማካሄድ ባቀዱት በተቃውሞ ሰልፉ የትግራይ ግዛት ማስከበር ፣ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው መመለስ የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች እንደሚያነሱ ገልፀዋል ፓርቲዎቹ።

የፓርቲዎቹን መግለጫ ተከትሎ የመቐለ ከተማ አስተዳደር ነሃሴ 25/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የተመረጠው ጊዜ አዲስ አመትና ሃይማኖታዊ በዓላት የሚበዙበት በመሆኑ ለማስተናገድ የማይመች ነው ሲል ከልክሏል። በተጨማሪም በበዓሉ በሚኖረው የህዝብና የመኪና ሰፊ እንቅስቃሴ ምክንያት በሚፈጠር የስራ መደራረብ ምክንያት ሰልፉን ማካሄድ ለማካሄድ እንደማይቻል የከተማ አስተዳደሩ ገልጧል።

ይህንን ተከትሎ ሶስቱ ፓርቲዎች ለከተማ አስተዳደሩ መግለጫ ትላንት ነሃሴ 26 ቀን በሰጡት ምላሽ ሰላማዊ ሰልፉ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማስፈፀም አንችልም ማለታችሁ ውድቅና የማንቀበለው ነው ብለዋል። ሰላማዊና ለውጥ ፈላጊውን ህዝባችን ይዘን በያዝነው የግዜ ሰሌዳ ሰልፉን እንደምናካሂደው ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን ሲሉም ገልፀዋል፡፡

አክለውም ለተመቸውና ላለው በዓል ይሁን እንጂ፣ ህዝባችን እንዲህ አይነት በዓላትን ማክበር ካቆመ ሦስት አመት እንደሆነው ፤ በዓል ማክበር ይቅርና በህልውና ጥያቄ ውስጥ እንደሚገኝ ፤ በማያባራ ጥፋት እንጂ  ፤ እንደ የስርአቱ ተጠቃሚ አካላት ተመችቶት እንዳልሆነ እንረዳለን ሲሉ ገልጸዋል። በመሆኑም የፀጥታ ስራ እንድታከናውኑና ትኩረታችሁን ደግሞ ከሰርአቱ ከሚሰነዝር ጥቃት ህዝቡ መታደግ መሆን እንዳለበት ደግመን እንገልፃለን ሲሉ ለከተማ አስተዳደሩ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡ አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button