ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ምክር ቤቱ በስድስት ወራት ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ ሰባት ውሳኔዎችን ማስተላለፉንና 15 አዋጆችን ማጽደቁን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1/2016 ዓ.ም፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ የአማካሪ እና አስተባባሪ ኮሚቴዎች አቅርቦ ውይይት እንደተካሄደበት ተጠቆመ።

ምክር ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከቀርበውለት 23 ረቂቅ አዋጆች ውሰጥ አንድ ደንብን ጨምሮ 15 አዋጆችን ማጽደቁን የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ምስራቅ መኮንን የምክር ቤቱን የስድስት ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት መናገራቸው ተጠቁሟል።

የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም እንዲሁም የግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጆችን ጨምሮ ሌሎች አዋጆች በቀጣይ ስድስት ወራት ምክር ቤቱ መክሮባቸው የሚጸድቁ መሆናቸውንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ምክር ቤቱ በዚህ ስድስት ወራት ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ ሰባት ውሳኔዎችን ማስተላለፉን፣ ዶ/ር ምስራቅ በሪፖርታቸው ለኮሚቴዎቹ ማቅረባቸውን መረጃው አመላክቷል።

ምክር ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ474 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ305 ምርጫ ክልሎች ተመራጮች ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ውይይት አድርገዋል ያለው የምክር ቤቱ መረጃ በተደረገው የመራጭ ተመራጭ ውይይት 1733 የሚሆኑ ጥያቄዎች ከህዝቡ መሰብሰባቸውን፤ ለ48 ተቋማት ጥያቄዎቹ ተልከው 47ቱ ተቋማት ምላሽ መስጠታቸውን አስታውቋል።

በፖርላማ ዲፕሎማሲ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፖ፣ ከምስራቅ አፍሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የባለብዙና የሁለትዮሽ ውይይቶች መደረጋቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል ያለው የምክር ቤቱ መረጃ ከሀገራቱ ጋር በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁሟል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button