ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ያደረገው ሰላም ስምምነት በሁለት ጎራ የከፈለው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1/ 2016 ዓ/ም፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አልተመዘገበም፣ ቅድመ ምርጫ እውቅናም የለውም ነገር ግን በትግራዩ ጦርነት ወቅት ግን ከትግራይ ሀይሎች ጋር አጋር ሆኖ በመሰለፍ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ እንዲታይ አድርጎታል፤ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን)።

የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ የአገው ህዝብ ጥቅምን “በትጥቅ ትግል” አስከብራለሁ ብሎ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች ከመንግስት ጋር ሲዋጋ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) መስራቾች የአገው ብሔራዊ ሸንጎ የዋግ ህምራ ዞን ስራ አስፈጻሚዎች የነበሩ መሆናቸውን እና መስራቾቹ “የሰላማዊ ትግል ምህዳሩ ሲጠብባቸው እንዲሁም ግፉ ሲበዛባቸው” ጠመንጃ አንስተው የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ይገልጻሉ።

በትግራይ ክልል ለሁለት አመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግስቱ መካከል በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ “ከትግራይ ኃይሎች ጋር በአጋርነት ሲዋጋ የነበረው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ህልውና ምን ይሆን?” የሚሉ ጥያቄዎች በወቅቱ ሲነሱ ነበር። 

ነፍጥ አንግቶ መንግስት ጋር ሲዋጋ የቆየው አዴን በክልሉ ዋግኽምራ ዞን 19 ያህል ቀበሌዎች መቆጣጠሩን በክልሉ መንግስት አካላት ሳይቀር መገለጹ አይዘነጋም። 

ይህን ተከትሎም ባሳለፍነው አመት የክልሉ መንግስት ታጣቂ ቡድኑ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ከንቀናቄው ጋር ሶስት ግዜ ንግግር አድርጓል። “ነገር ግን ንግግሩ ሽምግልና እንጂ ውይይት ባለመሆኑ” ከክልሉ መንግስት ጋር ድርድር ካልሆነ በስተቀር ሽምግልና እንደማይቀበል የንቅናቄው የውጭ ግንኙነት እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ መምህር ባየ በሬ ለአዲስ ስታንዳርድ ከአመት በፊት አስታውቀው ነበር።

ንቅናቄው በወቅቱ ሽምግልናውን ለለመቀበሉ “በሽምግልና ዘላቂ ሰላም የመፈጠር እድሉ ዝቅተኛ ነው” የሚል ምክያት አቅርቦ ነበር።  

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሁለተኝነት የተጠቀሰው ደግሞ “ የኛ ትግል የህዝቡን ነባራዊ ሁኔታ የተሻለ ለማድረግ እና ክልል ለመመስረት ነው፤ ስለዚህ ድርድር እንጂ የሽምግልና ሂደት የአገውን ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ለማምጣት የሚበጅ ባለመሆኑ ነው የማንቀበለው” ሲል ንቅናቄው ምላሽ ሰጥቶ ነበር።

ነገር ግን ከዘጠኝ ወራት በኋላ ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙን ንቅናቄው እና የክልሉ መንግስት አስታውቀዋል። ከስምምነቱ ጥቂት ቀናት በኋላም የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች ሹመት እንደሚሰጣቸው እና በማንነታቸው ምክንያት ከስራ የተባረሩ የመንግስት ሰራተኞች ወደ ነበሩበት እንደሚመለሱ ሊቀመንበሩ ማስታወቃቸውን ዶይቸ ቨለ ዘግቧል። ሊቀመንበሩ በጉዳዩ ዙሪያ የጠየቅናቸው ሊቀመንበሩ “ውሽት” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አስተባብለዋል።

ነገር ግን የስምምነቱ ፊርማ ሳይደርቅ ከንቅናቄው አመራሮች በኩል በስምምነቱ ዙሪያ አለመስማማቶች መከሰታቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች መውጣት ጀመሩ። አፍሪካን ኢንተሌጀንስ የተሰኘ ድረገጽ ይዞት የወጣው ዘገባ ደግሞ ይበልጥኑ “ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት በፈረመው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች መካከል ክፍፍል ተፈጠረ” ሲል ገልጿል።

የድርድሩ ሂደት እና  የተፈጠረው የአቋም ልዩነት መነሻ

የንቅናቄው የውጭ ግንኙነት እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እና የድርድሩ ተሳታፊ የነበሩት መምህር ባየ በሬ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ድርድሩ የተጀመረው በመከላከያ ሠራዊት በኩል ነው። የንቅናቄው ሊቀመንበር ኪሮስ ሮምሃም ይህንኑ አረጋግጠውልናል። 

ንቅናቄው ወደ ድርድር ሲገባ በዋናነት ኢጋድ አደራዳሪ እንዲሆን እና “ክልል መሆን” የሚለውን ለማሳካት መሆኑን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል። ነገር ግን “ኢጋድ በድርድር አፈጻጸም ውጤታማ አለመሆኑን በመረዳት ከመከላከያ ጋር ድርድር መጀመሩን” ጠቅሰዋል። 

ከመከላከያ ጋር የተጀመረው ድርድር እና ውይይት ላይ በመግባባት በአዴን እና በክልሉ መንግስት መካከል እንዲደረግ መወሰኑን አመላክተዋል። 

ከአማራ ክልል መንግስት ጋር በአዲስ አበባ ለሁለት ዙር ያክል ከተነጋገርን በኋላ “ስምምነት የሚመስል ነገር” ላይ መደረሱን የገለጹት መምህር ባየ በወቅቱ የተደረሰው ስምምነት “በተደራዳሪዎች እንደ ግለሰብ እንጂ በድርጅት ደረጃ ቀርቦ አቋም የተያዘበት አልነበረም” ሲሉ ገልጸዋል።

የንቅናቄው ሊቀመንበር ኪሮስ ሮምሃ ግን በዚህ አይስማሙም፤ “ሁሉም የንቅናቄው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሁለት ሶስት ግዜ መክሮ፣ ተስማምቶበት ነው የተፈረመው” ባይ ናቸው። እንዲያውም “ከ19ኙ የንቅናቄው አባላት 18ቱ ተስማምተውበታል” ሲሉ ይገልጻሉ። 

የንቅናቄው የውጭ ግንኙነት እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ መምህር ባየ በሬ በበኩላቸው ከ19ኙ የማዐከላዊ ኮሚቴው ውስጥ 18ቱ የተስማሙት የሰላም አማራጩን እንቀበለ በሚል እንጂ በሊቀመንበሩ በኩል የተፈረመውን ሰነድ አይደለም ሲሉ ያስተባብላሉ። ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ብቻ “በትጥቅ ትግላችን እንቀጥል በመንግስት በኩል የሚቀርበው የድርድር እና የሰላም አማራጭ አያዋጣንም” ሲል ከመጀመሪያው ተቃውሞና ልዩነቱን አንጸባርቋል ሲሉ ያብራሩት መምህሩ የተቀረው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ግን “እንስማማለን ነገር ግን ይሄ ይሄ ከተሟላ በሚል የስምምነት ነጥቦቹ አስቀምጦ ነው” ተልዕኮ የተሰጠን ብለዋል።

ከተደራዳሪው አካል አንዱ ነበርኩ ያሉን መምህር ባየ፤ ማዕከላዊ ኮሚቴው የተስማማውና ያጸደቀውን ስምምነት ለማድረግ ስንሄድ “ቅድመ ሁኔታዎች ተሰጥተውን ነው ” ሲሉ ይገልጻሉ።

መምህር ባየ አክለው እንደገለጹት፤ ሊቀመንበሩ ስምምነት ላይ የደረሱት የማዕከላዊ ኮሚቴው ካስቀመጣቸው ነጥቦች በታች በሆነ ሁኔታ ነው። “የስምምነቱን ነጥቦች ይዘው ሄደው አይደለም አጸደቅን የሚሉት፣ እኔን ጨምሮ በርካቶች ስላልተስማማንበት ክርክር ላይ ባለንበት ወቅት ነው ሊቀመንበሩ በራሳቸው ወስነው ስምምነቱን የፈጸሙት ሲሉ” ተቃውመዋል።

ሊቀመንበሩ ኪሮስ ሮምሃ በበኩላቸው ለድርድር ስንዘጋጅ ዋና ብለን ያስቀመጥነው [ነጥቦች፣ ቅድመ ሁኔታዎች ] እንዳለ ሁሉ የመጨረሻ ብለን ያስቀመጥነውም ነበር ሲሉ ገልጸው ስምምነቱ የተፈረመው በዚህ አግባብ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጨምረውም ስምምነት ላይ የደረስነው በጥናት ተመርኩዘን ነው ያሉት ሊቀመንበሩ ሁሉም የንቅናቄው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሁለት ሶስት ግዜ “መክሮና ተስማምቶበት” ነው የተፈረመው ብለዋል።  ስምምነቱ “ሁሉንም አሽናፊ የሚያደርግ” ነው ብለዋል።

ስምምነቱን እስከ መጨረሻ እየፈረሙ መጥተው የወጡ ግለሰቦች አሉ ያሉት አቶ ኪሮስ፣ ነገር ግን “ከፈረሙ በኋላ አንቀበልም ብለው ወጡ፤ በምክንያትነት ያቀረቡትም ነግር የለም” ሲሉ አስታውቀዋል።

ጥለው ወጥተዋል የተባሉት ሶስት ሰዎች መሆናቸውን እና “የንቅናቄውን ማህተም እና አንዳንድ ንብረቶች” መውሰዳቸውን የገለጹት ኪሮስ ሮምሃ፤ “ባይሳካም በተደጋጋሚ እንዲመለሱ ጥረት መደረጉን እና የወሰዱትን ንብረት ስላልመለሱ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እና እንዲባረሩ ማዕከላዊ ኮሚቴው መወሰኑን” ገልጸዋል። 

የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ ሊቀመንበሩ “በድርድር እኔ ክልል እሰጥሃለሁ በሚል የሚቀመጥ ህጋዊ ግራውንድ የለም” ሲሉ ገልጸው “ህዝብ ነው የሚጠይቀው፣ በምክር ቤት ነው የሚጠየቀው። ምክር ቤት እንዲጠየቅ መንገዱን እንዲከፍት ነው የምታመቻቸው” ሲሉ ጠቁመዋል።

ልዩነት የፈጠረው የክልልነት ጥያቄ እና ትጥቅ መፍታት ጉዳይ

የህዝብ ግንኙነቱ ሃላፊ መምህር ባየ በሬን ጨምሮ ስምምነቱን የተቃወሙ የንቅናቄው አመራሮች በምክትል ሊመንበሩ መሪነት የተሰባሰቡ ሲሆን ስምምነቱ ምን ቢጎድለው ነው ያልተስማማችሁት ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄ መምህር ባየ ሲመልሱ ለፊርማ የቀረበው ሰነድ ላይ “ላቀረብነው የክልልነት ጥያቄ እውቅና አይሰጥም፣ ቢያንስ በዚያ ዙሪያም አያጠነጥንም” ብለዋል።

“እኛ የጠየቅነው ህገመንግስታዊ ጥያቄ ነው፤ እራስ በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ ጥያቄ፤ ስምምነቱ ለዚህ እውቅና አይሰጥም፤ መቼ እንዴት ማንን ይጠይቃል የሚል ነገር አልተቀመጠም” ሲሉ ጉድለት ነው ብለዋል።

ቢያንስ በብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤቱ የክልልነት ጥያቄው አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ በምክር ቤት መጽደቅ አለበት የሚል ነው አንስተን የነበረው ያሉት ባየ፤ “እነሱ ግን ይህንን ለማድረግ ፍቃደኛ  አለመሆናቸውን ይህ በዋናነት ካልተነሳ ሌላው ትርጉም የለውም ብለዋል።

ሁለተኛው ደግሞ እንደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተወያይተን ያጸደቅነው ትጥቅ ለመፍታት ቅድመ ሁኔታዎች መቀመጥ አለባቸው የሚል ነው ያሉት መምህር ባየ፤ “ዝም ብሎ ትጥቅ ፍቱ ሳይሆን መንግስትም የተስማማንባቸው ነገሮችን ለመተግበር ፍላጎቱም እና ትግበራውን እያየን ነው ወደ ትጥቅ መፍታት የምንገባው የሚል ቢቀመጥም፤ ያ ሊሆን አልቻለም” ብለዋል።

ቢያንስ ትጥቅ ለመፍታትም ሆነ በሰላማዊ መንገድ ለመታገልም ከነበረው የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር መፈጠር አለበት የሚል ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የስምምነቱ ሰነድ ጠመንጃችሁን አስቀምጣችሁ ወደ ቀድሞ ኑሯችሁ ተመለሱ የሚል ይዘት አለው ሲሉ ገልጸዋል።

በነዚህ ምክንያቶች ምክትል ሊቀመንበሩ የሚመራው ቡድን፤ “ስምምነቱ፣ ሰላም መኖሩ  መልካም ቢሆንም፤ ነገር ግን ጥያቄያችንን በዘላቂነት እስካልፈታ ድረስ  ትክክል አይደለም፤ ጥያቄያችንን በሚፈታ መልኩ እንደገና መምጣት አለበት የሚል አቋም ይዘን ቀጥለናል” ብለዋል።

በክልሉ መንግስት በኩል የተቀየረ ነገር ምን አይታችሁ ነው የትጥቅ ትግልን ትታችሁ ሰላማዊ ትግል የመረጣችሁት? ስንል የጠየቅናቸው ሊቀመንበሩ ኪሮስ ሮምሃ ዋናው እና መሰረታዊው የክልሉ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩ ማስፋቱ መሆኑን ገልጸዋል።

“መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት በማንነታቸው ምክንያት ከስራ የተባረሩ ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱ ያደርጋል። በዚህ መሰረት የመንግስት ሰራተኛውንም ስም ዝርዝር አዘጋጁ እየተባልን ነው፤ መድረክ፣ ውይይቶች እየተደረጉ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ዋናው ቁምነገር እንደ አገው በትጥቅ ትግል ጥያቄያችን መመለስ አንችልም የሚል ነው ሲሉ ያመላከቱት ሊቀመንበሩ “ጦርነት ስትከፍት የምትዋጋው ከሚሊሻው ጋር ነው፣ ሚሊሻው አገው ነው፤ ጠላት አይደለም ብለዋል። ሚሊሻው በማያውቀው ነገር ነው እየተዋጋ፣ እሳት ውስጥ እየገባ ያለው። ስለዚህ ይሄንን መፍታት የምንችለው በሰላማዊ መንገድ ወደ ውስጥ በመግባት ነው በሚል ውሳኔ ላይ ደርሰን ነው ያደረግነው” ብለዋል።

በየክልሉ መንግስት በኩል ለአመራቹ ሹመት እና ጥቅማጥቅም ይሰጣቸዋል የተባለውን በተመለከት ሊቀመንበሩ ይህ ውሸት ነው ስልጣን ይሰጣችኋል አልተባልንም” ሲሉ አስተባብለዋል። “በግልጽ ለመናገር የክልሉ መንግስት ለመስማማት ፍላጎት አልነበረውም እንደ ሀገር የተቀመጠ አቅጣጫ ስላስገደደው ነው ለድርድር የተቀመጠው” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ስለዚህ ለመስማማት ያልፈለገ አካል ለምንድን ነው ገንዘብ መክፈል፣ መደለያ ገንዘብ የሚሰጠው ሲሉ ጠይቀዋል።

“ክልሉ ፋኖን እጅ ስጥ እያልኩኝ ከአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር አልደራደርም ብሎ አቋም ይዞ ነበር” ያሉት ኪሮስ ሮምሃ በምን አግባብ ገንዘብ ይሰጣል ብለዋል።

ሁለተኛ ሹመት የሚባል ነገር የለም፣ ሰነዱ ላይ የተቀመጠው የአዴን አመራሮች ከሹመት ውጪ ባሉት በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ ቦታ ይሰጣቸዋል ነው እንጂ የሚለው እንዲያውም በቅንፍ ውስጥ ከሹመት ውጪ ነው የሚለው፤ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

“አከባቢው የተረጋጋ ስላልሆነ በጋራ እናስተዳድር ብለን ጥያቄ አቅርበን ነበር፤ የተወሰነ ተቋም ስጡን ብለን ጠይቀን ነበር” ያሉት የአዴን ሊቀመንበሩ፤ “እናንተን ስለማናምን እና በብልጽግና የተቃኘ ሰው ስለሆነ ሹመት የሚያሰጠው ስንባል፣ ተውት ብለን መለስን። ነገር ግን ከሹመት ውጭ፤ ባሉት ተቋማት ላይ አስከ ክልል ቦታ ይሰጣል” ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ያሉበት ደረጃ ?

የታጠቀ ሀይል አለኝ ብሎ በረሃ ወርዶ ሲዋጋ የነበረው ሀይል የት ነው ያለው  በምን ሁኔታስ ላይ ይገኛሉ ስንል የጠየቅናቸው ሊቀመንበሩ ኪሮስ ሮምሃ “ታጣቂዎቹን እኔ እራሴ ወርጄ አወያይቻለሁ፣ 100 ፐርሰንት በሚባል ደረጃ ነው የተስማማው፣ ሰራዊቱ ደስተኛ ነው” የሚል ምላኝ ሰጥተዋል።

ሰራዊቱ ላይ መሳሪያ አወራረዱ ላይ ብዥታዎች እንደነበረ የጠቆሙን ሊቀመንበሩ በአሁኑ ወቅት ብዥታው ሁሉም ተስተካክሏል ብለዋል።  ወደ ቦታችን እንመለስ፣ ወደ ካምፕ እንግባ፣ አፋጥኑት የሚል ጥያቄ ከሰራዊቱ በኩል ተጠይቀናል ሲሉ የጠቀሱት “የክልልነት ጥያቄ፣ የማንነት ጥያቄ ጎን ለጎን ይጠየቅ፣ እኛ ጥይት መተኮስ አንፈልግም እያለ ነው” ሲሉ የሳራዊቱን አቋም አጋርተዋል።

በሌላኛው ጎራ ላይ ያሉትን መምህር ባየን የሚደግፋችሁ ወይንም ከጎናችሁ የተሰለፈ ሰራዊትስ አለ? ስንል ለጠየቅነው ጥያቄ ሲመልሱ አዎን አለ ሲሉ ገልጸው እኛ ጋር ያለው ሀይል እራሱን አደራጅቶ በራሱ ቦታ ተቀምጦ ነው ያለው ብለዋል። 

በሊቀመንበሩ በኩል ያሉትን የሰራዊቱን ሁኔታ በተመለከት መምህር ባየ ወደ መንግስት የገባው አካል ያነጋገር የሰራዊት አካል አለ እናውቃለን፣ ነገር ያ አካል ሙሉ በሙሉ እምነቱ ጥያቄያችን ሳይመለስ ትጥቅ አንፈታም የሚል ነው፤ ነገር ግን የመረጃ ክፍተት ስላለበት ማለትም ብቸኛ የሚያገኘው መረጃ ከመዋቅር የሚወርድለትን እና አንዳንዱ ፕሮፓጋንዳ ስለሆነ የተጣራ መረጃ እስኪያገኝ ድረስ ነው ብለዋል።

በትግራዩ ጦርነት ወቅት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የትግል አጋር ሆኖ ሲዋጋ የነበረው አዴን ከምስረታው እስከ አሁን ባለበው ጉዞ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት አላቸው። ታዲያ በትግራይ ክልል በኩል ስምምነቱ ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረት አለ? ስንል ሊቀመንበሩን ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ በትግራይ መንግስት በኩል ስምምነቱን የሚያደናቅፍ ነገር የለም፤ እንዲያውም እነሱ ናቸው በፕሪቶርያ ህግ ነው የምንገዛው፣ እናንተም ብትችሉ እኛ ጋር ካልሆነም እራሳችሁን ችላችሁ ተደራጁ የሚል አቅጣጫ የሰጡን” ብለዋል።

ኪሮስ ሮምሃ “ነገር ግን ያፈነገጡትን ግለሰቦች የሚያበረታቱ አሉ” ሲሉ ገልጸዋል።  “በትግራይም በኩል ቢሆን የግለሰቦች ጫናዎች አሉ፤ ድርጅት ብትሆኑ ጥቅም ታገኛላችሁ በሚል የሚደልሉ አሉ፤ እኛም ይህንን ሪፖርት አድርገናል” ሲሉ አስታውቀዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button