ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ ከባድ ማህበራዊ ቀውስ በማሰከተል ላይ ያለው የአማራ ክልል የትጥቅ ትግል ለምን ወደ ሰላማዊ  የፖለቲካ ትግል መምጣት ተሳነው?

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2016 ዓ/ም፦ የፌደራሉ መንግሥት በመደበኛ ሠራዊት ደረጃ ሰልጥነው በመደራጀት ተጠሪነታቸው ለየክልሎቻቸው ያደረጉ የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌዴራልና በክልል መደበኛ የጸጥታ ኃይሎች ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ መልሶ ለማደራጀት ያሳለፈውን ውሳኔና ትግበራ ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱት ተቃውሞዎች፣ የጸጥታ መደፍረስ እና ግጭቶችን መካሄድ ከጀመሩ ዘጠኝ ወራት አልፈዋል። 

“ክልሎች የራሳቸውን ልዩ ኃይል አደራጅተው እና አስታጥቀው ማሰማራታቸው ለአገር ደኅንነት አደጋ ነው ፤ አደረጃጀቱም ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው” በማለትም  ለአምታት በርካታ ተቃውሞ ሲደረግ መቆየቱ ይታውሳል።

የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ የኢትዮጵያን «ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት» የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀት ሥራ መሰራት ማስፈለጉን አስታውቆ ተግባራዊ አድርጓል። የፌደራሉ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ መከላከያ እና ፖሊስ ኃይል ለማካተት ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የኃይሉ ባለቤት በሆኑ ክልሎች በሰላማዊ መንገድ ውሳኔው ተግባራዊ ሲደርግ በአማራ ክልል ግን ተቃውሞ አጋጥሟል። ውሳኔውንም በመቃወም በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ውስጥ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።

መንግስት ውሳኔውን ማስተላለፉን ተከትሎ በአማራ ክልል በ2015 ዓ/ም ግንቦት መገባደጂያ ጀምሮ፤ በተለይም በቆቦ፣ በባሕር ዳር፣ በወረታ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን እና በመራዊ የተቃውሞ ሰልፎች፣ መንገድ መዘጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እንዲሁም በጸጥታ ኃይሎች መካከል ፍጥጫዎች መከተታቸው ተመላክቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች በተካሄዱ ግጭቶች በጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎችና በተፈጸሙ ጥቃቶች የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞችን ጨምሮ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት አስከትሏል። በሌላ በኩል በእነዚህ ከተሞችና ሌሎችም አካባቢዎች በተፈጠረው ውጥረት፣ አለመረጋጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እና የእንቅስቃሴ እገዳዎች ምክንያት በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ እና ሥራ ላይ እንቅፋት ሲያስከተል ቆይቷል፡፡

በወቅቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዳለ ተናግረዋል። ውሳኔውን በማስፈጸም በኩል በተፈጠረ ክፍተት እና “በተነዛው ፕሮፖጋንዳ” ችግሮች መከሰታቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ይህም በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን እና “ቅሬታው የመነጨው በተሟላ መንገድ ለሕዝቡ መረጃ ባለመድረሱ” መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማዋቀር እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ በሰዓቱ ባወጡት መግለጫ። “ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን” ተግባራዊ እንደሚደረግ እና ከዚህ አንጻር “ሆን ብለው የአፍራሽ ሚና በሚጫወቱ ላይ፤ ተገቢው የሕግ ማስከበር እርምጃ” እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከዚያን ግዜ ጀመሮ አማራ ክልል የተሰቀሰው የትጥቅ ትግል ተበብሶ በመቀጥል ከክልሉ አቅም በላይ መሆን ችሏል። በዚህም  የአቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፣ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እስክ ታችኛው መዋቀር ድረስ የስልጣን ለውጥ እና ሽግሽግ ተደርጓል። ይሁን እንጂ በክልሉ የተቀሰቀሰው ቀውስ ማብቂያ አላገኘም። 

በአማራ ክልል በረካታ አካባቢዎች በመንግስት እና በፋኖ ታጣቂ ኃይሎች መካከል እየተሄደ ያለው ግጭት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ በትጥቅ ትግል ለመፍታት ያለመ ይመስላል። በክልሉ እያተካሄደ ያለው የነፍጥ ትግልም ለበረካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥና መስተጓጎል ሲያስከትል በአጠቃላይ ህዝቡን ለከፋ ማህበራዊ ቀውስ ዳርጎታል። 

ሲሳይ አሳምሬ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እጩ ዶ/ር ናቸው። መምህር ሲሳይ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የአማራ ክልል የፖለቲካ ምህዳር ቀወስ ውስጥ ነው ሲሉ” ገልጸው፣ የአማራ ህዝብ እና ፖለቲከኞች ጥያቄዎቻችን በሰላማዊ መንገድ መልስ ያገኛሉ የሚለው እሳቤ በአማራ ልሂቃን እና በህዝቡ ዘንድ የነበረው ተስፋ “የተሟጠጠ” ይመስላል ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ አሁን ላይ የክልሉ ፖለቲከኛም ሆነ ህዝቡ በአርምሞት ላይ ነው ያለው። “የብልጽግናው መንግስት በብቸኝነት በአማራ የፖለቲካ ሜዳ እየቦረቀበት ይገኛል” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱም የማይበጅ ጤናማ ያልሆነ አካሄድ ነው ሲሉ ተችተዋል።

የአማራ ህዝብ እና ፖለቲከኞች በሰላማዊ መንገድ ላለመታገላቸው አንደኛው ምክንያት “የዘመናት ጥያቄያቸው የውሃ ሽታ በመሆኑ ነው” ፡ ሲሳይ አሳምሬ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር

“የአማራ ህዝብ በለውጡ ሰሞን ለብልጽግና መንግስት ትልቅ ድጋፍ የሰጠው፣ ጥያቄዎቼ ይመለሱልኛል በሚል ነበር” ሲሉ የጠቀሱት የፖሊቲካል ሳይንስ መምህሩ፤ “ህዝቡ ጥያቄዎቼ ፍትሃዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ይሰጣቸዋል ብሎ ጠብቆ ከድጡ ወደ ማጡ በሚመስል መልኩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማራዎች የሚፈናቀሉበት፣ ንብረቱ የሚዘረፍበት፣ እንደዜጋ የማይቆጠርበት፣ የሚዋረድበት እና ለተጨማሪ ችግሮች የተዳረጉበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል” ብለዋል።

“የህዝቡ ነባር ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ሌሎች ችግሮች ይደርስበት ጀመር” ሲሉ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ “ከማዕከላዊ መንግስቱ የበለጠ የመገፋት እርምጃ ተወሰደበት፤ የበለጠ መፈናቀል መሞት እና በፌደራል መንግስቱ የመካድ ተግባራ ተፈጸሙበት፤ እነዚህ የበለጠ ተስፋ ስላስቆረጡት ከፍተኛ የሆነ መሰረታዊ የፖለቲካ አመለካከት ለውጥ በአማራ ፖለቲከኞችም ሆነ በአማራ ህዝብ ተፈጥሯል፤ ይህ አመለካከት ነው ወደ ዝምታ የመራው” ሲሉ አስረደተዋል።

የአማራ ህዝብ እና ፖለቲከኞች በሰላማዊ መንገድ ላለመታገላቸው አንደኛው ምክንያት “የዘመናት ጥያቄያቸው የውሃ ሽታ በመሆኑ ነው” ብለዋል። ህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎችን የሚጠይቅበት “የአርምሞ ወቅት ላይ” ይገኛል ያሉት መምህሩ የአማራ ሙሁራን መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛሉም ብለዋል።

ሁለተኛው ደግሞ “የብልጽግና መንግስት የኢትዮጵያን ችግር እየፈታበት ያለው መንገድ በአማራ ሙሁራን እና ፖለቲከኞች ላይ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ነው” ይላሉ። “የአማራ ህዝብ ጥያቄ አሁን መልኩን ቀየር በማድርግ የህልውና ጥያቄ አድርጎታል፣ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቼ አይመለሱም የሚል አማራጭ ይዟል። ታይቶ በማይውቅ ሁኔታ ስቴትሁድ ጥያቄዎች ብቅ ማለት መጀመራቸውን ማየት ይቻላል” ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ ስም የሚንቀሳቀሱ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ

በክልሉ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የት ገቡ ስንል የጠየቅናቸው ረዳት ፕሮፌሰሩ “እንደእኔ እምነት እነሱም በዚህ መንግስት ተስፋ ቆርጠዋል” ሲሉ ገልጸው “መንግስት ጸጥ ለጥ አድርጌ ማስተዳደር እችላለሁ የሚል ስሜት ውስጥ መግባቱን ስለተረዱ ነው ከመናገር የተቆጠቡት” ብለዋል።

“መንግስት ምህረት የለሽ እንደሆነ ገብቷቸዋል፣ ሊታሰሩ አልያም እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ተረድተዋል” ሲሉ አብራርተው፤ ሀሳባቸውን የተናገሩ የክልሉ ፖለቲከኞች አሁን የት እንዳሉ ያውቃሉ፣ ከክልሉ ምክር ቤት አባላት እስከ የሀገሪቱ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ያሉት ታስረዋል፤ ይህን እያዩ እንዴት ይንቀሳቀሱ፣ ፍራቻ የፈጠረው ድባብ አለ ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ እየተወሰደ ያለው ወታደራዊ ትግል ውጤት

በአማራ ክልል ከሚያዚያ ወር መጀምሪያ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት እና አለመርጋጋት አድማሱን በማስፋት ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን የክልሉ መንግስት ሳይቀር አስታወቋል። የክልሉ መንግስት በአማራ ክልል በትጥቅ የተደገፈ ጥቃት መፈጸሙንና የተፈጠረውን አለመረጋጋት በመደበኛው የህግ ሥነ ሥርዓት ለማስከበርና ለመቆጣጠር ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል። ይህንን ተከትሎ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራሉ መንግስት ስድስት ወር የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ 

በዚህም መከላከያ ሰራዊት ወደ ክልሉ በመሰማራት ከፋኖ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ግጭት በመካሄድ ላይ መካሄድ ከጀመረ ዘጠኝ ወራት አልፈዋል። መንግስት በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን አልመረጋጋት እና ግጭት ለማስቆም እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ቢገልጽም በዚህ ሁሉ ግዜ ውስጥ ክልሉ ወደ ቀድሞ ሰላሙ ሙሉ ለሙሉ መመለስ አልቻለም። በዚህም የተነሳ በክልሉ የተለያየ መጠን ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችን ጨመሮ በርካታ የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ ተቋማት አስታውቀዋል።  

በክልሉ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸው እና በጥቃቱ የበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቧል።  መንግስት በክልሉ በወሰደው የአየር ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ህዳር 7/ 2016 ባወጣው መግለጫ አስታወቋል፡፡ ድርጅቱ በጥቃቱ ኢላማ ከተደረጉ ቦታዎች ማካከል ትምህርት ቤትና መነሃሪያ ይገኝበታል ሲልም ገልጿል።  

በተጫማሪም አዲስ ስታንዳርድ በአማራ ክልል በርካታ ወረዳዎች በተፈፀመ የከባድ መሳሪያ እና ድሮን ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን እና ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይም ውድመት መደረሱን ነዋሪዎችን ዋቢ በማደረግ ሲዝግብ ቆይቷል። እንዚህ በክልሉ የተቀሰቀሰው ግጭት ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት ለመሆኑ ጥቂት ማሳያዎች ናቸው። 

የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ “መንግስት ታንኩንም ድሮኑንም ጭኖ ወደ ክልሉ ገብቷል፣ ነገር ግን በመሳሪያ የሚፈታ የክልሉ ችግር የለም” ብለዋል። ይህ ትግል የሚቀጥል ከሆነ “ክልሉን በማውደም እና እንደ ሀገር ደግሞ ክስረትን በማስከተል የሚጠናቀቅ ትግል” ነው የሚሆነው ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል። መምህሩ እንደሚሉት “መንግስት ጦርነቱን ማሸነፍ እንኳ ቢችል፣ የክልሉን ፖለቲካ ግን ማሸነፍ አይችልም”።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለጽ በመጠየቅ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ ወታደራዊ ባለሞያ፤ በበኩላቸው “መንግስት በትግራይ ላይ የተከተለውን ወታደራዊ አካሄድ በአማራ ክልል ላይም ከወሰደ አደጋው ሰፊ ነው” ሲሉ ያሰረዳሉ።  ይህም የሚሆነው የአማራ ክልል ከትግራይ ክልል ስፋት እና የህዝቡ በዛት የሚበልጥ በመሆኑ በአማራ ክልል ላይ የሚካሄዱት ወታደራዊ እርምጃዎችን ከባድ ስለሚያደርገው ነው በለዋል።

“የክልሉ አርሶ አደር አኩርፏል፣ ባሳለፍነው የግብርና አመት ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርም አለመቅረቡ ተጽእኖ ፈጥሮበታል ይህም ወደ ትገል ሊያስገባው ይችላል” ፤ ወታደራዊ ባለሞያ

የክልሉ ቀጣይ እጣ ፋንታ 

የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በትኩረት የሚከታሉት ወታደራዊ ባለሞያው፤ የክልሉ ቀጣይ ሁኔታ በዋናነት ቀጣይነት ያለው “ቀውስ የሚሰፍንበት” ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። “በክልሉ እየተካሄደ ያለው አመጽ በማዕከል ደረጃ የሚዘውረው መሪ የለሌለው መሆኑ ለዚህ ዋነኛ ግብአት እንደሚሆን” ጠቁመዋል።

“በክልሉ የመንግስት ተዓማኒነት ሞቷል ሊባል የሚችል ነው” ያሉት ወታደራዊ ባለሞያው “መንግስት ከ20 ሚሊየን የክልሉ ጠቅላላ ህዝብ ጋር ነው የተጣላው፤ ደጋፊ የምትለው ሀይል የለውም፤ ማንቸውም የሚያመጣቸው ሀሳቦች ሁሉ መገዳደር ይገጥመዋል” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

በክልሉ በአሁኑ ሰአት ያለው ተቃውሞ የአርሶ አደሩ ተቃውሞ ይመስላል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ምልከታቸውን ያጋሩት ባለሞያው “የክልሉ አርሶ አደር አኩርፏል፣ ባሳለፍነው የግብርና አመት ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርም አለመቅረቡ ተጽእኖ ፈጥሮበታል ይህም ወደ ትግል ሊያስገባው ይችላል” ብለዋል።

በክልሉ ተቃውሞ ሲጀመር የክልሉን መንግስት ያንገዳገደው እና የፌደራል መንግስቱን ጣልቃ ገብነት እንዲጠይቅ ያደረገው እንቅስቃሴው የአርሶ አደሩ ስለነበረ ነው ሲሉ የሚሞግቱት ባለሞያው አሁን በአማራ ክልል ከፍተኛ ተጽእኖ ያመጣው የአርሶአደሩ እንቅስቃሴ መኖሩ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ሰላም እንዲመጣ ክልሉ ሌላ ቅርጽ ሊይዝ ይገባል በሚል ጨዋ ቋንቋ የሚገልጹ፣ አለፍ ሲልም ጠንቀር ባለ አገላለጽ መፍረስ አለበት የሚሉ አስተያየቶች መሰንዘ ጀምረዋል። በታወጀው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ላይ ደግሞ የተቋቋመው ዕዝ የተለያዩ አስተዳደር እርከኖች እና መዋቅሮችን መልሶ ማቋቋም፣ ማደራጀት የሚል ስልጣን ተሰጥጦታል በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የጠየቅናቸው ወታደራዊው ባለሞያው “ክልሉን ሌላ ቅርጽ ማስያዝ ላይ ከባድ ይሆናል ሲሉ ገልጸው መንግስት ይሄን ካደረገ እራሱን በራሱ የማጥፋት ሙከራ ይመስለኛል፣ ምክንያቱም ፌደራሊዝሙ ነው ይሄንን የፈጠረው፣ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ክልሉን ሌላ ቅርጽ ልትያስይዘው አትችልም” ብለዋል።

የተለየ አስተዳደራዊ መዋቅር ለማድረግ ከተንቀሳቀሰ የብሔርተኝነት ስሜቱን ከማጋጋል እና ከመላተም በስተቀር የሚያስገኘው አወንታዊ እረባና አይኖረውም ሲሉ አብራርተዋል።

እጩ ዶ/ር ሲሳይ እንደሚሉት፣ መንግስት ግብር እየሰበሰባ አይደለም፣ ህግ እና ስርአት የለም፣ የመንግስት አገልግሎቶች እየተሰጡ አይደለም፣ ትምህርት ተቋርጧል፣ የፍትህ ተቋማይ በአግባቡ ስራ እየሰሩ አይደሉም። በዚህ ሁኔታ “ክልሉ የሚቀጥልበት” መንገድ አይኖርም በለዋል። 

በአሁኑ ወቅት በክልሉ “የፓርቲ ስርዓት እየጠፋ” ያለ ይመስላል ያሉት ሲሳይ፣ “አብን የለም፣ አማራ ብልጽግና የለም” ሲሉ ገልጸው ህዝቡ የፓርቲ ድንበር ሳይበግረው፣ የዕምነቶች ልዩነት ሳይለያየው “የህልውና አደጋ ላይ ነን” ብሎ በማመኑ በጋራ የቆመ ይመስላል ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተውናል። 

ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ “በእኔ ግምት አማራ ብልጽግና ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ ከህዝቡ ትግል ጋር ናቸው፣ ያለ አማራ ብልጽግና ፓርቲ እገዛ እና ድጋፍ የክልሉ ተቃውሞ እዚህ ደረጃ ይደርሳል፣ እንዲህ ጠንክሮ ይወጣል የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል።

በውጭ ያለው ዳያስፖራም” ከመንግስት ያልተናነሰ” ባጀት መመደብ የሚችል ሀይል መሆኑን ጠቁመው ይህም ግጭቱ በቀላሉ እንዳይበርድ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button