ዜናፖለቲካ

ዜና፡ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰተው ውጥረት እና ግጭት ከመባባሱ በፊት አስቸኳይ ምላሽ ይሻል ሲል ኢሰመኮ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2016 .ም፡ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰተው ውጥረት እና ግጭት ከመባባሱ በፊት አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) ዛሬ ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተለይም ከአካባቢ አስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአከባቢው ነዋሪዎች እና የመንግስት አካላት መካከል ውጥረት መድፈኑን አስታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ነዋሪዎችን፣ የመንግሥት አስተዳደር እና ጸጥታ ኃላፊዎችን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ውትወታ ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቁሟል።  

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በአካባቢው እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገሩ፤ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድን ተከትለው እንዲፈቱ ለአካባቢው የመንግሥት አስተዳደር፣ ለአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ሁኔታው ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመላክቷል።

በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙርያ ወረዳ ሥር የሚገኙ ኤልጎ፣ ወዘቃ፣ ደምብሌ እና ጫሞ 01 የተባሉ አራት ቀበሌዎች ከጋሞ ዞን በመውጣት ልዩ ወረዳ ሆነው ለመደራጀት በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተው የነበረ ሲሆን በተለይ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ውዝግቡ እየተባባሰ እንደመጣ ጠቁሟል።

ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና በጋሞ ዞን አስተዳደር መካከል ያለው አለመግባባት ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን አመላክቷል።

በተለያዩ ሰዎችና ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች የነዋሪዎች የሙዝ እርሻዎች እና በመንግሥት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ንብረት ማውደም ጉዳት መድረሱን ያስታወቀው ኢሰመኮ በተለይም ከኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በግለሰቦች እና በጸጥታ አካላት በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ለጊዜው ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ነዋሪዎች እና የጸጥታ አባላት ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን አመላክቷል።  

እንዲሁም በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ውጥረት፣ ግጭት እና እየተወሰዱ ያሉ የኃይል እርምጃዎች በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳያስከትል ያላቸውን ስጋት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ መግለጻቸውን አካቷል።

“የፌዴራል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከዞኑ አስተዳደር እንዲሁም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በአፋጣኝ ውጥረቱን የሚያረግብ ሰላማዊ እርምጃዎች መውሰድ እና ዘላቂ መፍትሔ ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ማሳሰባቸውንም ገልጿል።

ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች መጠየቃቸውንም ጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button