ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በመዲናዋ በተካሄደ ኦፕሬሽን ከአንድ ሚሊዩን በላይ የሶማሌላንድ እና የበርካታ ሀገራት ገንዘቦች ከነ-ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የሚመራው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ከጥር 17 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄዱት የ7ኛው ዙር የተቀናጀ ኦፕሬሽን የተገኙ ውጤቶችን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በዝርዝር አስታውቋል።

ፖሊስ ተገኙ ብሎ በዝርዝር ከገለጻቸው ስኬቶቹ መካከል በሕገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 28 ሺህ 5 መቶ 42 የአሜሪካ ዶላር፣ 34 ሺህ 4 መቶ ዮሮ፣ 34 ሺህ 155 የካናዳ ዶላር፣ አንድ ሚሊዮን 8 መቶ 35 ሺህ 4 መቶ 10 ብር፣ አንድ ሚሊዩን 150 ሺህ የሶማሌላንድ ገንዘብ እና በርካታ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ከነ-ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራው እየተደረገባቸው ነው የሚለው ይገኝበታል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመከላከያ ሰራዊት እየወሰደ ባለው እርምጃ መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን ጨምሮ በፅንፈኛ ኃይሎች ሲል የጠራቸው ታጣቂ ሀይሎች አባልት ናቸው ብሎ የገለጻቸውን እና ሸሽተው አዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ተደብቀው ነበር ያላቸውን 53 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሏል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥም መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን ናቸው የተባሉ 37 እና የፅንፈኛው ቡድን አባላት ናቸው ሲል ፖሊስ የገለጻቸው 16 ሰዎች ከተለያዩ ከደበቋቸው የጦር መሣሪያዎች፣ ትጥቆችና ሚስጥራዊ ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ሥር ውለዋል ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገ ፍተሻ 14 ሕገ-ወጥ ክላሽንኮቭ ጠመንጀ ከመሰል 1500 ጥይቶችና 5 ካርታ ጋር፣ 15 ልዩ ልዩ ሽጉጦች ከ158 መሰል ጥይት ጋር መያዙን ከፌደራል ፖሊስ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የአዲስ አበባን ሰላምና ደኅንነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተካሄደ ያለው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን “ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ነው” ያለው መረጃው በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብን ያማረሩ ወንጀሎች “በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሱ መጥተዋል” ብሏል።

ከዚህም ባሻገር ከወንጀል ፈፃሚዎች ጋር በመመሳጠር የፖሊስን መረጃ ለተጠርጣሪዎች አሳልፈው ሲሰጡ የነበሩ እና በሌሎች ጥፋቶች ላይ የተገኙ 146 የፖሊስ አመራሮችና አባላት ላይ አስተማሪ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የፀጥታና ደኅንነት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሥራ መመሪያ መሰጠቱን፤ ኅብረተሰቡም የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የአትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ጥሪ ማቅረባቸውን መረጃው አካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button