ዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ ከቀናት በፊት ዘጠኝ አማኞቿ የተገደሉባት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ድርጊቱን አወገዘች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2016 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ዘጠኝ አማኞቿ ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም የተገደሉባት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ አወጣች።

የተፈጸመው በደል እንዲጣራና አጥፊዎቹ ወደ ህግ እንዲቀርቡ ያደርጉ ዘንድ የፌደራል እና የክልል መንግስት አካላትን ጠይቃለች።

ድርጊቱ የተፈፀመው ከ10 ቀናት በፊት ቢሆንም እስካሁን መግለጫ ያላወጣሁት መንግስት ሀላፊነቱን ይወጣል፡ አጣርቶ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል በሚል ነው ስትል ገልጻለች።

በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ መነ ሃሞ በመባል በሚታወቀው ቀበሌ “ቶኩማ መነ ሃሞ” በተሰኘ የመካነ ኢየሱስ ማህበረ ምዕመናን ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ በቤተ ክርስቲያን በጸሎት ላይ ከነበሩት 17 ሰዎች መካከል ማንነታቸው ተጣርቶ ባልታወቀ ታጣቂዎች 9 የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ላይ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል ብላለች።

ግድያው የተፈጸመባቸው አባላቶቿ ከፖለቲካ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ንጹሐን ዜጎች ናቸው ያለችው ቤተክርስቲያኗ የተፈጸመው ጭካኔን የተሞላ ዘግናኝ ድርጊት ነው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በጽኑ ታወግዛለች፤ ኃዘንዋንም ለመግለጽ ትወዳለች ብላለች፡፡

ቤተክርስቲያኗ በመግለጫዋ ከዚህም በፊት በተለያዩ ቦታዎች በተመሳሳይ በአማኞቿ ላይ ግድያ መፈጸሙን አውስታ በአብነትም ባለፈው አመት በምስራቅ ወለጋ በሳሲጋ ወረዳ 15 የቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን በዕሁድ የአምልኮ አገልግሎት ላይ እያሉ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በጅምላ መገደላቸው፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቦጂ ወረዳ በዕሁድ አምልኮ ላይ የነበሩ ሶስት ወጣቶች በታጣቂዎች መገደላቸው፤ እዲሁም በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በምእመናን ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶች እየተከሰቱ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡

ለነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለፍትህ ድምጽዋን ስታሰማ ብትቆይም ምላሽ የተሰጠበት አንድም ጊዜ አልነበረም ስትል ኮንናለች፡፡ 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ድርጊቱ ፈጻሚዎቹን ለይቶ ወደ ህግ ማቅረብና የዜጎችን የመኖር ሕገ መንግስታዊ መብት የማክበርና የማስከበር ሚና የመንግሥት ሃላፊነት መሆኑን በመግለጽ በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግስትና የክልሉ መንግስት ብርቱ ክትትል በማድረግ ህዳር 14/2016 ዓ/ም እና ከዚያም በፊት በአባላቶቻችን ላይ የተፈጸመው በደል እንዲጣራና አጥፊዎቹ ወደ ህግ እንዲቀርቡ ስትል ጠይቃለች።

እንዲህ ላሉ ፈርጀ ብዙ ክስተቶች ዋና መንስዔ የሆነው በአገሪቱ ያለው የሰላም እጦት መሆኑን በመጥቀስ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመንቀልና ዜጎች ያለስጋት የሚኖሩባት፤ ከቦታ ወደ ቦታ በነጻነት የሚዘዋወሩባት እና ልማት የተረጋገጠባት አገር እንድትኖረን መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ እንዲያሳይና እርቅና ሰላም እንዲያሰፍን ጠይቃለች።

እርቅን፣ ሰላምንና አገራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ረገድ በሚደረገው ማናኛቸውም ጥረት የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብላለች። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button