ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በዳሬሰላም እየተካሄደ ባለው ድርድር ጥሩ ሂድት መታየቱን ተከትሎ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች የወታዳራዊ መሪዎቹን ወይይት ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 3/ 2016 ዓ ም፦ በፌደራል መንግስቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛንያ ዳሬሰላም እየተካሄደ ባለው ሁለተኛው ዙር የሰላም ውይይት ጥሩ ሂደቶች መታየታቸውን ለአደራዳሪዎቹ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚንስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በትላንትናው እለት ድርድሩን ተቀላቅለዋል፡፡ አንድ ምንጮቻችን ገለጻ፣ ይህ “በድርድሩም ሆነ በአደራዳሪ ቡድኑ ላይ የሚፈጥረውን መተማመን የሚያሳይ ነው”።

ድርድሩ መጀመሩን ተከትሎ ከቀናቶች በኋላ ሁለቱም ወገኖች ታሳቢ የተደረጉትን ዋና ጉዳዮችን ወደ መፍታት ደረጃ መሸጋገራቸውን አዲስ ስታንዳርድ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በታንዛንያ ዋና ከተማ በሆነችው ዳሬሰላም ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ከተጀመረው ውይይት ቀደም ብሎ የሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ወታደራዊ ሃላፊዎችን ያሳተፈ ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ስብሰባዎች የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሁለት ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተወካዮች ጋር በመሆን በአዲስ መልክ “ፖለቲካዊ ውይይት” አድርገዋል።

አዲስ ስታንዳርድ የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ዋቢ በማድርግ እንደዘገበችው ቀደም ብለው ባደረጉት ድርድር ውጤታማ የተባለ የፖለቲካ ውይይት መስተዋሉ በመካሔድ ላይ ላለው ድርድር አስታውጽኦ አድርጉዋል፡፡ የዲፕሎማቲክ ምንጮቹ አክለውም ከሁለቱም ወገን ከሳምንታት በፊት በተካሄደው የፖለቲካ ውይይት ተካፋይ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ድርድሩ በስኬት ከተከናወነ ለፊርማ ስነስርአቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። 

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ በአምባሳደር ማይክ ሀመር የተመራ የአሜሪካ የልዑካን ቡድን እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የኬንያ እና የኖርዌይ መንግስታት ውይይቱን በማመቻቸት ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ  ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ውይይቱን በንቃት እያመቻቹ መሆኑን የአዲስ ስታንዳርድ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ኑር መሐመድ ሼክ በድርድሩ ላይ የኢጋድ ሃላፊ መኖራቸውን ባያረጋግጡም “የኢጋድ ዋና ፀሐፊ በሁሉም አባል ሀገራት ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ይገልፃል” ብለዋል። አክለውም  ኢጋድ እየተካሄደ ያለው ውይይት ጥረት ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስገኝ ተስፋ ያደርጋል ብለዋል።

ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር መንግስት ከ“ኦነግ ሸኔ” ጋር በዛንዚባር ከሚያዚያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ድርድር እንደሚያደርጉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የመጀመሪያው የድርድሩ ሂደት መጀመሩ ይታወሳል።

ጠ/ሚንስትር አብይ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር በታንዛኒያ ድርድር እንደሚጀመር መግለፃቸውን ተከትሎ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ መንግስት ሶስተኛ አካል ባለበት ድርድር ለማድርግ የቀረቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በመቀበሉ ድርድሩ እንደሚጀመር ማረጋገጡ በዘገባው ተካቷል፡፡

በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በታንዛኒያ የተካሄደው ድርድር ሳምንት ያክል ከፈጀ በኋላ ከስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በወቅቱ በመንግስት በኩል የሰላም ድርድሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ በሚል የተገለጸ ሲሆን ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ መከናወኑን በመግለጽ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡ ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል ብሏል መግለጫው።

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በበኩሉ ባወጣው ምግለጫ የመጀመሪያው የድርድሩ ምዕራፍ መጠናቀቁን ገልፆ በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጧል፡፡

ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በቀጣይ ተገኛኝተው ውይይቱን በማስቀጠል በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ግጭትን ለመፍታት መስማማታቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button