ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር በኩል የወደብ ባለቤት ለመሆን በጎረቤቶቿ ላይ ወረራ እንደማትፈጽም ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አመላከቱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ መንግስት 116ኛው ዓመት የመከላከያ ሠራዊት በዓል “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም አክብሯል። በበአሉ ላይ የተገኙት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በሃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር የለም ሲሉ ገልጸዋል።

ከቅርብ ግዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ውይይት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ስታነሳ ወረራ ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ይደመጣል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በንግግራቸው  ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በዚሁ በተከበረ ቀን መግለጽ የምፈልገው ኢትዮጵያ በሃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር የለም ብለዋል።

ለጋራ ጥቅም ለጋራ እድገት ለጋራ ብልጽግና ሁሉንም አሸናፊ ለሚያደርጉ ጉዳዮች ከወንድሞቻችን ጋር ተወያይተን የጋራ ጥቅም ለማስከበር እንጥራለን ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር አብይ በሀይል ፍላጎቶቻችን ማሳካት ወንድሞቻችን ላይ ቃታ የምንሰነዝር እንዳልሆን በአጽንኦት ለረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ከማስከበር፣ ሰላም ከመጠበቅ የሀገር ብልጽግና እንዲቀጥል ከማድረግ ውጭ የሆነ አላማ የለው ሲሉ አስታውቀዋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button