ዋና ትረካ

ትረካ፡ የአይን ብርሃን ማጣቱ ከምግብ አዘጋጅነት ሙያው ያላቆመው አይነ ስውሩ ምግብ አብሳይ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15 /2015 ዓ.ም፦ አካል ጉዳተኝነት ቀላል አይደለም። በተለይ በድገተኛ አደጋ የሚፈጠር አካል ጉዳተኝነት፣ ጉዳት በደረሰበትም ሰው ሆነ በአከባቢው በሉ ሰዎች ላይ የሚፈጥረው የስነልቦና ጉዳት ቀላል ባለመሆኑ በአሉታዊ መንገድ የህይወትን አቅጣጫ ሲቀይር ይስተዋላል። በዛው ልክ በድንገተኛ አደጋ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ተስፋ ባለመቁረጥ የጀመሩትን የህይወት ጉዞ የሚያሳኩም እየተበራከቱ መጥተዋል። ለዚህ ደግም ምስክር ከሚሆኑት መካከል ሼፍ ዳንኤል ከበደ አንዱ ነው። 

ባለትድር እና የሶስት ልጆች አባት የሆነው ዳንኤል ከበደ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቤላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ዳንኤል ከአነደኛ  እስከ ስድስተኛ ክፍል ቀበና በሚገኘው ኪዳነምህረት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በመቀጠልም በቀድሞ ስሙ ቢትውድድ በአሁን ስያሜው የካ ምስራቅ ጮራ ስባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ተምሯል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ምስራቅ አጠቃላይ ኮምፕርሄሲቨ የሙያ ትምህርት ቤት በመግባት ሆም ኢኮኖሚክስ ተከታትሏል፡፡ ዳንኤል ቀጥሎም ተፈሪ መኮንን ቴክኒክ እና ሙያ ት/ቤትን በመቀላቀል ልሶስት አምታት በምግብ ዝግጅት እና ጥናት ዲፕሎማውን አግኝቶ በሙያ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

ዳንኤል ከበደ በምግብ ዝግጅት ስራ ለ25 አምታት ቆይቷል፡፡ የአይን ብርሃኑን በድንገት ያጣው ዳንኤል ይህን ሙያ አይን ስውር ሆኖም እየክውነው ይግኛል፡፡ አይኖቹ ማየት ባይችሉም አጅግ ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን ከመስራት ግን ያስቆመው ነገር የለም።

ክስትቱ የተፈጠርበትን ምክንያት ሲያስርዳ “ከልጅነት ጀምሮ የስኳር ህመም ታማሚ ነኝ በዚህም የተንሳ የህክምና ክትትል አደርግ ነበር፤ ከዛ አንድ ቀን ከስራ ውጥቼ ክትትል ወደማደርግበት የህክምና ተቋም ሄድኩኝ፤ ደምስርህ አብጧል ስለዚህ የጨረር ህክምና ይደረግልህ ተብየ ተደረገልኝ፤ ነገር ግን ህክምናው የማየት ችሎታዬን በማድክም ለአይኖቼ ብርሃን መጥፋት ምክንያቱ ሆኑ” ሲል ተናግሯል፡፡ 

በህክምና ስህተት የአይኑን ብርሃን ማጣቱን የሚገልጠው ዳንኤል በድንገት የአይን ብርሃኑን ማጣቱ ከባድ ግዜያትን እንዲያሳለፍ አድርጎታል፡፡

ይህንንም ሲያስርዳ “እያየ የነበረክ ሰው በአንድ ጊዜ አለማየት ውስጥ ስትገባ ራሱን የቻለ ከባድ ተፅህኖ አለው፤ ያ ጊዜ በጣም ከባድ ነበር፤ ለመግልጽም ይከብዳል፡፡ እንደገና ደሞ የአካባቢህ ሰዎች ያንን አለመቀበል በጣም በጣም ፈተና ነበረው” ብሏል:: 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ዳንኤል በዚም አላበቃም “ከአልጋ ተነስተህ ሽንት ቤት መሄድ ያቅትሃል፤ ድሮ የምታውቀው ነገር ሁሉ ይጠፋሃል፤ ሳሎን መግባት ያቅትሃል፤ እንኳን ደጅ ወጥተህ ሥራ ልትሠራ እና ከማህበረሰቡ ጋ ልትቀላቀል፣ የምታውቅው የቤትህ መውጫ በር ይጠፋሃል፣ እንደገና ደግሞ ማህበረሰቡ ከንፈር ሲመጥልኝ በጣም ነበር የሚጎዳኝ በጣም። አንዳንዶች ደግሞ ምንም ላያደርጉልህ ቅስምህን የሚሰብሩ ንግግሮች ይናገራሉ፤ ግን አሁን ታሪክ ሆኖ አልፏል” ሲል የደረሰበትን ፈተና አስረድቷል።  

በዋና ምግብ አዘጋጅነት በማገልግል ላይ የነበረው ዳንኤል ባገጠመው ድንገተኛ አደጋ ተስፋ ቆርቆ ወድቆ መቅረትን እንደ አማራጭ ሳይወስድ አሁን ላይ ካሰበው ለመድረስ በርካታ ስራዎይን በማከናወን ላይ ይገኛል። “አሁን ላይ እንኳን ለራሴ ለሌላም ተርፊያለዉ” ሲል ገልጿል።

ባላሰበው ድንገተኛ አደጋ የአይኑን ብርሀን ካጣ በኋላ ካለበት ጭንቀትና ድንጋጤ ወጥቶ የህይወት ጉዞውን በርትቶ እንዲቀጥል ካገዙት አንዱ የባለቤቱ ገጠመውን አደጋ ተቀብላ ባህሪዬ ሲለወጥ ያንን መቻሏ ነው ይላል። የልጆቹ አጠገቡ መሆን በአካባቢው ያሉ ሰዎች መረዳት እንዲበረታ እንደረዳው ገልጿል። 

“ግን ከቤት እንድወጣ ያደረገችኝ የአለም ሎሬት  የትነበርሽ ንጉሴ ነች” ሲል የሚገልጸው ሼፍ ዳንኤል የትነበርሽ ባደረገችለት በስነልቦና ምክር ድጋፍ አንድ ርምጃ እንድሄድ ረድቶኛል ሲል ስለ ብርቱዋ ሴት ይመሰክራል። 

በኋላ ላይ እኔም ራሴንም ማጠንከር እንዳለብኝ ውስጤ ተሰማኝ የሚለው በዚህም ውሳኔው በራሱ ነገሮችን ማድረግ ይጀምራል። 

“ምግብ ማዘጋጀትም ሆነ ሌሎች ክንውኖችን፣ እንዲሁም ይመቸኛል ብዬ ማስባቸውን ነገሮች ራሴ ማዘገጃጀት ጀመርኩኝ። ከዛ በሁሉም ነገሮች ላይ ራሴን ዝግጁ እያደረኩ” ሲል እንዴት ነገሮችን በራሱ መንገድ ማከናወን እንደጀመረ አስረድቷል።

በህይወቴ እኔ የሰራሁት ሥራ አንድና አንድ በምግብ ዝግጅት ነው ሲል የተናገረው ሼፍ ዳንኤል አደጋው እስከደረሰበት ግዜ ድረስ በዋና ምግብ አዘጋጅነት ሙያ በተለያዩ ሆቴሎች ሰርቷል።

ዳንኤል አሁን ላይ አይኖቹ ማየት ባይችሉም አጅግ ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን ግን ከመስራት አላስቆሙትም። 

የአይን ብርሃኑን ካጣ በኋላም አይኖቼ ማየት ስለማይችሉ ምግብ አዘጋጅ መሆን አልችልም ብሎ ያልተቀመጠው ዳንኤል ከአደጋው በፊት በመኖሪያ ቤቱ ምግብ የሚያዘጀበትን የማብሰያ ቦታ ጠንቅቆ ማወቁ አይን ብርሃኑን ካጣ በኋላ መግብ መስራት አስችሎታል።

ዳንኤል ቤቱ ምግብ ለማዘጋጀት ምንም አይቸግረውም፣ ምን የት እንደማገኝ በማወቁ ሁሉንም ለረጅም አመታት ካገኘው ልምድ በመነሳት በእጆቹ አየዳሰሰ የተለያዩ ምግቦችን ይሰራል።  

ለእኔ የሚከብደኝ ዠ  ጋዝ ማቀጣጠል ነው ምክንያቱም የቱ ጋር እንደሚነድ መለየት ስለሚከብድ ሊያቃጥል ስለሚችል ነው ሲል ይናገራል። በተረፈ ግን ሌላው ነገር በግማሽ ሰዓት ወይም አንድ ሰዓት አዘጋጆቶ መጨረስ እንደሚችል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።

በሙያው ካለው ልምድ ሽንኩርት፣ ቲማቲምን የመሣሰሉ ግብዓቶችን በቀላሉ በእጅ በመዳበስ ማወቅ ይችላል። ቅመማ ቅመሞችንም በማሽተት ይለያል። የማይሸቱትን፤ ለምሳሌ ጨው ስኳር የመሳሰሉትን በመቅመስ ለይቶ ይጠቀማል። “የረጅም አመት ልምዱ ስላለኝ አሳ ከዶሮ ሥጋ የመለየት ብቃቱ አለኝ” የሚለው ሼፍ ዳንኤል የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምግቦችን ይሰራል። 

“አካል ጉዳተኞች ወይም ዓይነ ስውራን እንደምንችል እኔ ማሳያ ነኝ። እንሠራለን እንለወጣለን፣ እንችላለን፤ መሥራት እና ራሳችንን መመገብ እንችላለን አልፎ ተርፎም ለሰዎች እንተርፋለን” ሲል አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ምክር ለግሷል። 

ሰዎች በሥራ ቦታዬ ላይ ሲያዩኝ የሚሠጡኝ አስተያየት ከእኔ አለፎ ሌሎችን አነቃቅቷል የሚለው ዳንኤል “አካል ጉዳተኝነትን ከውስጣችን አግዝፈን ስለምንመለከተው ነው እንጂ ካመንን ሁሉንም ነገር መሥራት እንችላለን” ብሎ ያምናል።

ወደዚህ ሙያ ለመግባት ለሚሹም አስፈላጊው ነገር ፍላጎት ነው መሆኑን፤ ነገር ግን ፍላጎት ከሌላቸው የሚገጥማቸውን ፈተናዎች እንዱሁም ሙያው የሚፈልገው ለሰዓታት ቆሞ መስራትን ተቋቁመው መስራት አይችሉም ብሏለ።

አካል ጉዳት የሌለበትም ሰው ሆነ አካል ጉዳተኛ እችላለሁ በሚል መንፈስ ፍላጎቱን ካስቀደመ ምንም ነገር መሥራት ይችላል ሲል አክሏል።

የአይኖቹን ብርሃኑን በማጣቱ ብዙዎች ኃዘኔታ ቢኖራቸውም ሊቀጥሩት ግን አለመፈለጋቸውን ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቆይታ የተናገረው ዋና ሼፍ ዳንኤል ከበደ በዚህም ምክንያት ከቤት ሆኖ እንዲሁም እየተንቀሳቀሰ የምግብ ማዘጋጀት ስራን ማደራጀት ጀምሯል። 

በአሁኑ ወቅትም ሆቴል የማደራጀት፣ የማማከር ስራን ይሰራል። ለተለያዩ ዝግጅቶች ማለትም ለሠርግ፣ ለልደት፣ ለድግስ እና ለስብሰባዎች የሚቀርቡ የምግቦችን የማዘጋጀት ስራን በመስራትም ገቢ እያገኘ ቤተሰቡን እያስተዳደረ ነው። እነዚህ ሥራዎች ላይ ዳንኤል በማደራጀት ብቻ ሳይሆን በማብሰልም ይሳተፋል።

በዚህም ስራ በስሩ እስከ 13 ለሚሆኑ ሠራተኞች ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥሮላቸዋል። “ሥራዎች ባሉ ሰዓት እነሱን ይዤ ነው የምንቀሳቀሰው፤ በቀን ከ2000 እስከ 3000 ለአንድ ሠው እከፍላለሁ። አይነስውር ብሆንም ከራሴ አልፌ ለሌሎች መትረፍ ችያለሁ” ብሏል። 

ዋና ሼፍ ዳንኤል እቅዴ የራሱን ሬስቶራንት የመክፈት እቅድ አንግቧል። “በትልቁም ባይሆን በትንሹ ባለኝ ነገር ላይ ተመሥርቼ ባለኝ ችሎታ እና ዕውቀት የራሴን ሬስቶራንት ከፍቼ መሥራት እፈልጋለሁ” ይላል።

“አሁን ላይ ከጨለማ ወጥቻለሁ ብዬ ነው የማስበው፤ ማንም ሠው ሙሉ አካል አለኝ ብሎ የሚኮራበት ጊዜ ላይ አይደለም ያለነው፤ እያንዳንዳችን ምን እደሚደርስብን አናውቅም። እኔ አሁን ሥጋዬ ላይ የደረሠው ጉዳት ነው እንጂ ውስጤ በርትቷል፤ ሁሉም ሠው አልችልም የሚል መንፈስ እንዳይኖረው! በህይወታችን ምንም ቢፈጠር ነገን መቀበል እና መቀጠል ያስፈልጋል። ምንም ነገር ቢሆን ይቻላል። ይህም የተሻለ ዕድል ይዞልኝ እንደ ሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ከቤት ያወጣኝ እግዚአብሔር ነውና እርሱንም በጣም አመሠግነዋለሁ!” ሲል መልዕክት አስተላልፏል።አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button