ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ኬንያ ከኢትዮጵያ በግዢ የማገኘው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን በግማሽ ቀንሶብኛል ስትል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ እየሸጠችልኝ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል የስምምነታችንን ግማሽ ብቻ ነው ስትል ኬንያ ገለጸች።

ከኢትዮጵያ ጋር በፈጸምኩት ስምምነት መሰረት የምገዛው የኤሌክትሪክ መጠን 200 ሜጋ ዋት የነበረ ቢሆንም በምሰራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በግድቦች ያለው የውሃ መጠን በመቀነሱ እና በቂ ኤሌክትሪክ ለማምረት ባለማስቻሉ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ብቻ በመግዛት ላይ እገኛለሁ ብላለች።

የኬንያ የሀይል አቅርቦት ካቢኔት ዋና ጸሃፊ ዴቪስ ቺርቺር እንዳስታወቁት በምስራቅ አፍሪካ አሳሳቢ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት የኤሌክትሪክ ክፍያ መጠን ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሯል ሲሉ መናገራቸው ቢዝነስ ደይሊ አፍሪካ በድረገጹ አስነብቧል።

የኬንያው ማሲንጋ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ባለፉት ሁለት ወራት በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ውሃ ባለማግኘቱ ምንም አይነት ኤሌክትሪክ ማመንጨት አለመቻሉን ሃላፊው ጠቁመዋል።

ከሳምንታት በፊት ኬንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአጎራባቾቿ ሀገራት የገዛችው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት በሶስት እጥፍ ማደጉን ማስታወቋን መዘገባችን ይታወሳል። የኬንያ በውሃ ሀይል የምታመነጨው የኤሌክትሪክ መጠን በግድቦቿ የውሃ መጠን ማነስ ምክንያት ከፍተኛ ቅናሽ በማሳያቱ ሳቢያ ከአጎራባቾቿ ሀገራት በመግዛት ለማካካስ መጣሯን ቢዝነስ ደይሊ አፍሪካ ድረገጽ ዋቢ በማድረግ በዘገባው አካተናል። በ2022 ነሃሴ ወር ላይ ከአጎራባቾቿ ሀገራት የገዛችው የኤሌክትሪክ መጠን 208 ነጥብ 47 ሚሊየን ኪሎዋት አዎር ሲሆን በተያዘው 2023 ነሃሴ ወር ላይ ግን መጠኑ 185 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን እና የገዛችው የኤሌክትሪክ መጠን በአሃዝ 594 ነጥብ 01 ሚሊየን ኪሎዋት አዎር መሆኑም ተመላክቷል።

ኬንያ ከአጎራባቾቼ ሀገራት ገዛሁት ካለችው የኤሌክትሪክ ሀይል 70 በመቶ የሚሆነውን የገዛችው ከኢትዮጵያ መሆኑን ድረገጹ ከኬንያ መንግስት ያገኘውን ዳታ መሰረት አድርጎ አካቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button