ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የአማራ ክልልን “የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ነው” ሲል የክልሉ መንግስት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10/2016 ዓ.ም፡- “የአማራ ክልልን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ” በመሆኑ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጥሪ ማቅረቡን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን አስታወቀ።

ክልሉን “የብጥብጥ እና የሁከት ማዕከል” ለማድረግ የሚያስችል ተደጋጋሚ “የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር” በቁጥጥር ስር መዋሉን የኮሙዩኒኬሽን ቢሮው በማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ አመላክቷል።

የአማራ ክልልን ወቅታዊ “የፀጥታ ችግር ታሳቢ ያደረጉ” እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ “የሕገ ወጥ መሳሪያዎች ዝውውር” በፀጥታ ኃይሉ ጥብቅ ቁጥጥር መያዛቸውን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮን ዋቢ በማድረግ የገለጸው መረጃው የሕገ ወጥ መሳሪያ እና ተተኳሽ ዝውውሩ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ መከሰቱንም ተመላክቷል።

“መነሻውን መቀሌ ከተማ ያደረገ እና ስሚንቶ ከጫነ ተሽከርካሪ ላይ የተጫነ ሕገ ወጥ ተተኳሽ በፍላቂት ገረገራ ከተማ አስተዳደር ፖሊሶች ጥብቅ ክትትል” መያዙን የጠቆመው ቢሮው 10 ሺህ 385 የክላሽ እና የብሬን ተተኳሽ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል።

በሌላ በኩል “ከሀራ ተነስቶ ቆቦ ሁለት ቀናትን በማደር፤ ጋይንት ደርሶ ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ላይ ከጋይንት ተነስቶ ወደ ደብረ ታቦር ከተማ ሲደርስ በተደረገ ፍተሻ ሰባት ክላሽ እና 2009 ጥይት” በቁጥጥር ስር መዋሉንም አካቷል።

አንድ ሲኖ ትራክ “የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን ምርት ጭኖ ከቆቦ መስመር ወደ ደብረታቦር” ሲመጣ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሲሚንቶው ውስጥ 18 ሺህ 143 ጥይት በፍተሻ መያዙንም ጠቁሟል።

በተመሳሳይ አሸዋ ጭኖ “ከቆቦ ወደ ጋይንት መስመር” ሲጓዝ በደረሰ ጥቆማ በርካታ “ሕገ ወጥ ተተኳሾችን እና የኮንትሮባንድ እቃዎችን” እንደጫነ በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከዚህ ጋር በተያያዘም “የአማራ ክልልን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ” የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button