ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ አሜሪካ፣ ኢጋድ፣ ኬንያ እና ኖርዌ በዳሬሰላሙ የፌደራል መንግስቱ እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ውይይት ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም፡- የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የደቡብ እዙ መሪ ገመቹ ረጋሳ በታንዛንያ በመካሄድ ላይ ባለው የፌደራል መንግስቱ እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ውይይት ዳሬሰላም እንደሚገኙ ተገለጸ።

በዳሬሰላም በመካሄድ ላይ ያለውን የፌደራል መንግስቱ እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ውይይትን በማመቻቸት ረገድ እና በማወያየቱ ዙሪያ አሜሪካ፣ ኢጋድ፣ ኬንያ እና ኖርዌ ቁልፍ ሚና መጫወት ላይ እንደሚገኙ የአዲስ ስታንዳርድ ዲፕሎማቲክ ምንጮች አስታወቁ።

አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ዋና ተወካዯ ማይክ ሀመር በኩል ሚናዋን እየተጫወተች መሆኗን የጠቆሙን ምንጮች የኢጋድ ከፍተኛ ሃላፊዎች እንዲሁም የኬንያ እና ኖርዌ ተወካዮችም እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በፌደራል መንግስቱ በኩል በውይይቱ ተወክለው በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት የደህንነት ሃላፊው ጀነራል ጌታቸው ጉዲና እና በመጀመሪያው ዙር የታንዛንያው ድርድር ተሳታፊ የነበሩት ምክትላቸው ሜጀር ጀነራል ደምስ አሜኑ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።  

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በመወከል በውይይቱ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ደግሞ ስምንት ሰዎች ሲሆኑ አራቱ ከሰራዊቱ የምዕራብ እና ማዕከላዊ ኮማንድ በጃልማሮ እየተመሩ፣ ሁለት ከደቡብ የሰራዊቱ ኮማንድ በገመቹ ረጋሳ እየተመሩ እና በመጀመሪያው ዙር ሰራዊቱን ወክለው ከተሳተፉት ውስጥ ኢጀርሶ ኡርጌሳ እና ጂሬኛ ጉዴታ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የፌደራል መንግስቱ እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተወካዮች ውይይቱን እያካሄዱ የሚገኙት በዳሬሰላም በሚገኘው ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ጃል ማሮ የተካፈለበት በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል በዳሬሰላም ሁለተኛው ዙር የሰላም ውይይት መጀመሩን ምንጮቻችንን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በፌደራል መንግስቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛንያ ዳሬሰላም ሁለተኛው ዙር የሰላም ውይይት ትላንት ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ጉዳዩን ከሚከታተሉ ሁለት ዲፕሎማቶች አዲስ ስታንዳርድ ማረጋገጧ በዘገባው ተጠቅሷል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ጃል ማሮ በሶስተኛ ወገን አደራዳሪዎች አመቻችነት በምዕራብ ኦሮምያ ከሚገኝ ጫካ ወደ አቅራቢያው ወደሚገኘው የደንቢዶሎ አየር ማረፊያ እንዲበር መደረጉን ጠቁመው ከዚያም ወደ ድርድሩ ቦታ በተዘጋጀለት ሄሎኮፕተር መጓዙን ተናግረዋል። በዚህም ሂደት ጃል ማሮ ለመጀመሪያ ግዜ ከፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት መቻሉንም አመላክተዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ከምንጮቻ እንደተረዳችው ከሆነ ባሳለፍናቸው ሶስት ሳምንታት የፌደራል መንግስት እና የኦሮምያ ክልል መንግስት ከፍተኛ ሃለፊዎች እንዲሁም ሁለት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት ውጤታማ የተባለ የፖለቲካ ውይይቱ ተካሂዷል።

ውይይቱ ውጤታማ ስለነበር እና በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት ትላንት ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ምንጮቻችን ገልጸዋል።  

ከሁለቱም ወገን ከሳምንታት በፊት በተካሄደው በቀደመው የፖለቲካ ውይይት ተካፋይ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ድርድሩ በስኬት ከተከናወነ ለፊርማ ስነስርአቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button