ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በፋኖ ታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት 13 ሰዎች ተገደሉ

በአብዲ ቢያንሳ @ABiyenssa 

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4/ 2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ቆርቆቤ በሚባል አካባቢ፣ የደረሰ ሰብል ለማጨድ ወደ አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ በመጓዝ ላይ ባሉ ሰዎች ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ማክሰኞ ዕለት በፈጸሙት ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን የስፍራው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የወረዳው መምህር በፋኖ ታጣቂ ሀይሎች ማክሰኞ ታህሳስ 2 ቀን ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ የተገደሉት 13ቱ ሰዎች በቅርቡ በተፈጠር የጸጥታ ችግር ምክንያት ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ ጫቦ ቀበሌ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ሰብል ለመሰብሰብ ወደ ቡሬ ወረዳ በመጓዝ ላይ እያሉ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ከተገደሉት ሰዎች መካከል የቀን ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች እና ባላሃብቶች ይገኙበታል ሲሉ መምህሩ ገልጸዋል። 

መምህሩ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ታብሱሎ ዳሳሌ፣ ጫላ ዳጃሽ፣ ወርቃለም ስራህብዙ፣ ጃለታ ዘላለም፣ አራጎ መለሰ፣ ገዙ ተፈራ፣ ሞላ አዲስ እና አበበ ተመስገን የተባሉ ሰዎችን ጨመሮ 13 ሰዎች በጥቃቱ ተገድለዋል።

ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት የተገደሉት ሰዎች፣ ከምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ የተፈናቀሉ በኦሮሞ ተወላጆችን ሰብል ለመሰብሰብ በመጓዝ እያሉ መሆኑን አረጋግጧል።  

“ታጣቂዎቹ ንበረትነቱ ንጉሳ ባንጃ የተባለ ግለሰብ የሆነ፣ ሲኖትራክ የሚባል የጭነት ተሽከርካሪ በመምታት 13 ሰዎችን ገድለዋል። ሌሎች አራት ሰዎች ከተሽከርካሪው በመዝለል መትረፍ ችለዋል። የተጎጂዎችን አስከሬን ለማግኘት የቻልነው በቀሪዎቹ አራት ሰዎች የስልክ ጥሪዎች ነው” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የአሮሞ ነጻነት ግንባር የጸጥታ ችግርን እና በንጹሃን ላይ የሚደረግ ግደያ በማስመልከት ትላንት ባወጣው መግለጫ ቆርቆቤ በሚባል አካባቢ በ13 ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ገድያ አውግዟል። “ በንጹሃን ዜጎች ላይ ለሚፈጽሙ ዘግኛኝ ድርጊቶች ተጠያቂው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ነው” ሲል ከሷል። 

በማከልም ፓርቲው በመግለጫው “ መንግስት በቀጣይነት ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ለሚፈጸመው የሰበዓዊ ወንጀሎች ከህግ እና ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጥም” ሲል አክሏል።

ይህ እየተፈጸሙ ያሉት የመብት ጥሰቶች እንዲቆሙ የኦሮሞ ህዝብ፣ ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ ድርጅቱ ጥሪ አቀረቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button