ኢዲስ አበባ፣ ነሀሴ 28/ 2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል መስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ቅዳሜ ነሀሴ 25/ 2016 ዓ/ም በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉንና አንድ ሰው መቁሰሉን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
የኪረሙ ወረዳ ነዋሪ ደሳለኝ ፊለቴ ለአዲስ ስታንዳርድ፤ ጥቃቱ በኪረሙ ወረዳ መርጋ ጅሬኛ ቀበሌ “በፋኖ ታጣቂዎች” መፈጸሙን ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተገደሉት ሶስት ሰዎች ዘመድ የሆኑት ደሳለኝ፤ ግለሰቦቹ ከመርጋ ጅሬኛ ገበያ ወደ ዋስቲ ቀበሌ በመመለስ ላይ እያሉ መገደላቸውን ተናግረዋል።
የዋስቲ ቀበሌ አስተዳዳሪ ጥበቡ ሞሴ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ዘግይቶ በመድረሱ ግድያውን ማስቀረት አለመቻሉን ለአዲስ ስታንዳርድ አሳውቀዋል።
በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ሶስቱ ሰዎች እድሜያቸው በ40ዎች ውስጥ የሚገኝ፤ ረጋሳ ጎዶ፣ አመንቴ እና በላቸው ዳኘው የተባሉ ነዋሪዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ረጋሳ የአስር ልጆች አባት፣ በላቸው ደግሞ ሰባት ያላቸው ሲሆኑ እንዲሁም መርጋም በርካታ ልጆች ያላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ደሳለኝ፤ ጥቃቱ የሞቾች ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማስከተሉን ተናግረዋል።
አክለውም ሰዎቹ እሁድ ነሀሴ 26 ቀን በኪዳነ ምህረት በቤተ ክርስቲያ ስርዓተ ቀብራቸው መፈጸሙን ገልጸዋል።
ሌላኛው በጥቃቱ ጉዳት የደረሰበት የስድስት ለጆች አባት የሆኖት አቶ ደሳለ ጮኩሉ በአካባቢው ባለ የህክምና ተቋም የመጀመሪያውን የህክምና እርዳታ አግኝቷል።
“ነገር ግን ጉዳቱ ከባድ በመሆኑ ምክንያት ወደ ኪራሙ ሆስፒታል ከዚያም ወደ ጊዳ አያና ሆስፒታል ተላልፎ የነበሩ ሲሆን በኋላ ላይ ወደ ነቀምት ከተማ ሆስፒታል እንዲዘዋወር ተደርጓል” ሲሉ የተገጂው ዘመድ ገልጸዋል።
“የህግ የበላይነት አለመኖር በአካባቢው ነዋሪዎችና አርሶ አደሮች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው” ብለዋል።
ሌላኛው የመርጋ ጅሬኛ ቀበሌ ነዋሪ የደሳለኝን ስጋት በማስተጋባት በኪረሙ ወረዳ የሚገኙ የአካባቢው ባለስልጣናት ለህብረተሰቡ የደህንነት ጥያቄ ምላሽ አለመስጠታቸውን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
“ከኪረሙ አስተዳደር ጥበቃ ጠይቀን ነበር፤ ግን ግዴታቸውን መወጣት አልቻሉም” ያሉት ነዋሪው፤ “ይልቁንም በነዋሪዎች ላይ ፍርሀትን እየፈጠሩ እና ሰዎችን እንደ ኖኖ እና ሊሙ ካሉ ቀበሌዎች እያስወጡ ነው” ብለዋል።
ከ2015 ጀምሮ በአማራ እና ኦርሚያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ሲፈናቀሉ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
አክለውም ከአራት ወራት በፊት በሁለቱ ማህበረሰቦች [ በአማራ እና ኦሮሞ] መካከል የተደረገውን እርቅ ተከትሎ ብዙዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው የእርሻ ሥራቸውን እንደጀመሩ ተናግረዋል።
“በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ሲመለሱ ደህንነታቸውን የሚያስጠብቅ የፀጥታ አካላት በስፍራው አላገኙም” ብለዋል።
የዋስቲ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ጥበቡ በአካባቢው እርቅ ቢደረግም ከኪራሙ ወረዳ አስተዳደር ቁጥጥር ውጭ በሆነው በአማራ ክልል በኩል ትጥቅ አለመፈታቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አስተዳዳሪው የፋኖ ታጣቂዎች በአራት ቀበሌዎች ማለትም ዎፍጪ፣ ሀሮ፣ ዱቡቅ እና ጨፌ ጉዲና፤ የጦር ሰፈር በመገንባት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል። የስልጠና ማዕከላቸው በኪራሙ ወረዳ በጊን ቀበሌ ውስጥ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሰኔ ወር በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ አሮ ቀበሌ የፋኖ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለው ጥቃት ሶስት ንጹሃን ይህወት ማለፉን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ወር በታጣቂዎቹ በኪረሙ ወረዳ ወስቲ ቀበሌ ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት ስመንት ሰዎች ሲሞቱ 13 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።
መንግስት “ሸኔ” እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም በወረዳው በመትገኝ አሮ ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት አንዲት እናት ከሶስት ልጆቿ ጋር መገደሏን ነዋሪዎች ተናግረዋል። አስ