ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በዳራ ወረዳ በአንድ ወጣት ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ቁጣ ቀስቅሷል፤ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ43 በላይንፁሀን ተገድለዋል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12/2017 ዓ.ም፡- ከሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት ወዲህ በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨት ላይ ያለው የደራ ወረዳ ነዋሪ የሆነ የ17 አመት ወጣት አንገቱ ሲቆረጥ የሚያሳየው ቪዲዮ በርካቶችን ያሳዘነ፣ ቁጣን የቀሰቀሰ ተግባር ሁኗል።

አሰቃቂ ግድያውን የሚያሳይ ቪዲዮ ከመሰራጨቱ በፊት በአከባቢው በታጣቂዎች በሚፈጸም ተደጋጋሚ ጥቃት ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በጫካ ውስጥ የተደበቁ ሰዎች ፎቶግራፎች በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ዘዴዎች በስፋት ተጋርተዋል። 

አዲስ ስታንዳርድ በተያዘው ሳምንት በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨት ላይ ያለውን የዚህን ወጣት አሰቃቂ ግድያ ጉዳይ ማረጋገጥ ባይችልም የቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ባቀረበው ዘገባ አሰቃቂው ግድያ የተፈፀመው በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ላይ ነው። 

አንድ የወረዳው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት በታጣቂዎቹ አንገቱ ሲቀላ የሚታየው ወጣት ደረጀ አማረ የ17 እድሜ ያለው የደራ ወረዳ ነዋሪ ነው።

እንደነዋሪው ገለጻ “የወጣቱ ቤተሰቦች የሚኖሩት በወረዳዋ በምትገኘው ወረን ገብሮ በተባለች ቀበሌ ሲሆን ቪዲዮው አሁን ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይሰራጭ እንጂ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከሁለት ወራት በላይ አልፎታል። ድርጊቱን የፈጸሙት የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው” ብለዋል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኘው የደራ ወረዳ የጦርነት አውድማ ሆናለች፣ በወረዳዋ በመካሄድ ላይ ያሉት ግጭቶች ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል።

በተለይም ከ2015 በኋላ በመንግስት ሃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተደረጉ ከፍተኛ ውጊያዎች ወረዳዋን ወደ አሳዛኝ የግጭት ማዕከልነት ቀይሯታል፤ በዚህም የበርካታ የአከባቢው ነዋሪዎች ህይወት ተቀጥፏል፣  ማህበረሰቡን ለከፍተኛ ቀውስ ዳርጓል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከሐምሌ 2016 ዓ.ም በኋላ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በአከባቢው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ውጊያ መጀመራቸውን ተከትሎ በደራ ወረዳ በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት ወደ ለየለት ትርምስ አድጓል።

የደራ ወረዳ በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታ ላይ መገኘቷ የፍጥጫው ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል፤ በተለይም ደግሞ ከነሃሴ 17 2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጎ ግጭቶቹ ተባብሰው ነበር። በዚህን ወቅት በተለይም በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ከፍተኛ የሆነ ውጊያ ተካሂዷል።

ከሀምሌ ወር 2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ባሉት አራት ወራት ውስጥ በመንግስት ሀይሎች እና በታጣቂዎች መካከል በተደረጉ ግጭቶች ከ43 በላይ ንፁሀን ዜጎች ህይወት ማለፉን አዲስ ስታንዳርድ ከዳራ ወረዳ ነዋሪዎችን ያሰባሰበው መረጃ ያሳያል።

ለአብነትም በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ላይ በተፈጸሙ ሶስት የተላያዩ ግጭቶች ብቻ የሰባት ነዋሪዎች ህይወት ጠፍቷል። ነዋሪዎቹ የተገደሉት በፋኖ ታጣቂዎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መሆኑን የአይን ምስክሮች ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

የያዝነው አመት 2017 ዓ.ም መስከረም ወር በደራ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ የተስተናገደበት ነበር፤ በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመው በትንሹ የ17 ንጹሃን ዜጎች ህይወት አልፏል።

ከታጣቂዎች በተተኮሰበት ጥይት ከሞት ተርፎ በአዲስ አበባ “አቤት ሆስፒታል” ህክምና በመከታተል ላይ የሚገኘው ጋሪ ሃባቦ የተባለ ከየከባድ መኪና ሹፌር ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ከሱ ጋር ታግተው የነበሩ ሶስት ሹፌሮች እና አንድ ረዳት ተገድለዋል።

የግንባታ እቃዎች ጭነው ደራ ከተማ ላይ አራግፈው ወደ አዲስ አበባ በአማራ ክልል በኩል አድርገው በመመለስ ላይ እያሉ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ፈትራን በተባለች ቦታ አምስት የፋኖ ታጣቂዎች አስቁመው እንዳገቷቸው የገለጸው ጋሪ ሃባቦ አራት ሹፌሮች አራት ረዳቶቻቸው እና አንድ የአከባቢው ነዋሪ አጠቃላይ ዘጠኝ ነበር ሲል ገልጿል። ከሁለት ቀናት በኋላ ከሾፌሮቹ እና ረዳቶቹ ጋር ታግቶ የነበረው የአከባቢው ነዋሪ በታጣቂዎች መገደሉን አስታውቋል። ከስምንቱ ሹፌሮች እና ረዳቶቻቸው ውስጥ ሁለቱን ታጣቂዎቹ እንደለቀቋቸው እና ሌሎቹን ግን ለማስለቀቂያ ለእያንዳንዳቸው አንድ ሚሊየን ብር እንደጠየቁ አስታውሷል።     

ነገር ግ በኋላ ላይ ታጣቂዎቹ ተኩሰው ሶስቱን ሹፌሮች እና አንድ ረዳት እንደገደሏቸው እሱ ራሱ እግሩ ላይ እና ሆዱ ላይ በጥይት ተመትቶ የሞተ መስሏቸው ጥለውት እንደሄዱ አስታውቋል። እንደመታደል ሁኖ የአከባቢው ነዋሪዎች አግኝተውት ወደ ክሊኒክ እንደወሰዱት እና ከዚያም በአቤት ሆስፒታል ህክምና በማግኘቱ መትረፉን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።  

አዲስ ስታንዳርድ በደራ ወረዳ በተለያዩ ግዜያት በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል እንዲሁም በታጣቂዎቹ እና በመንግስት ሀይሎች በተካሄዱ ግጭቶች የተገደሉ ንጹሃንን እና የደረሱ ጉዳቶችን የተመለከቱ ዘገባዎች ማቅረቡ ይታወሳል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ አድዓ መልኬ ቀበሌ የገንዳ አረቡ መስጅድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ መኪን ሐጂአረፉ በታጣቂዎች ከታገቱ ከሳምንታት በኋላ መገደላቸውን ጥቅምት ወር መጨረሻ ባቀረብነው ዘገባ ተገልጿል፤ ግድያው የአከባቢውን ማህበረሰብ ክፉኛ ማስቆጣቱም በዘገባው ተካቷል፡፡

በተጨማሪም በኦሮምያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ታጣቂዎቸ በፈጸሙት አዲስ ጥቃት ሶስት ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ አንድ ነዋሪ መቁሰሉ የተመለከተ ዘገባ ተስተናግዷል፤ ጥቃቱን የፈጸሙት የፋኖ ታጣቂዎቸ ናቸው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ መናገራቸውም ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button