
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12/2017 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የፋኖ ታጣቂ ሀይሎች “ዘመቻ አንድነት” በሚል ስያሜ በተለያዩ የአማራ ክልል አከባቢዎች ያካሄዱትን የተቀናጀ ጥቃት በማክሸፍ ደምስሻለሁ ሲል መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የፋኖ ሀይሎች ዘመቻውን ያካሄዱት “በብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ሀይለና ግብረ አበሮቹ” አደራጅነትና አይዞህ ባይነት ነው” ሲል ወንጅሏል።
መከላከያ ሰራዊት ዛሬ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ የፋኖ ታጣቂ ሀይሎች በክልሉ በሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች ላይ ውድመት ፈጽሟል፣ የመንግስት መዋቅርን ለማፈራረስ ተንቀሳቅሷል ሲል ገልጿል።
መግለጫው በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፋኖ ቡድኖች “የአንድነት ዘመቻ” በሚል ስያሜ የተቀናጀ ዘመቻ መክፈታቸውን ተከትሎ የተሰጠ ነው።
በግጭት እየታመሰ ባለው የአማራ ክልል በአዲስ መልክ ባለፉት ቀናት ግጭቶች መቀስቀሳቸውን እና ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን የተመለከቱ ሪፖርቶች በመውጣት ላይ ይገኛሉ።
የፋኖ ሀይሎችን “ጽንፈኞች” ሲል የጠራቸው የመከላከያ መግለጫ በክልሉ “ጥቃት ከፍተዋል” ፤ በዚህ ክልሉን ለማተራመስ እየተደረገ ባለው “ዘመቻ አንድነት” በተሰኘው እንቅስቃሴ ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ሀይለ ከጀርባ አሉበት ሲል ወንጅሏል።
የፋኖ ሀይሎች “ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷባቸዋል” ሲል መከላከያ ሰራዊቱ በመግለጫው አስታውቋል፤ “ተደምስሰዋል” ብሏል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበ ሃይሌ “እድሜ ልኩን በታሪኩ ግጭት ተማቂ” ናቸው ሲል የኮነነው መግለጫው “ያለ ምንም ወታደራዊ ዕውቀት የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት” ሲያስገባ ነበር ሲል ተችቷል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ “ምዕራብ ትግራይን አስመልሳለሁ በሚል ሁለት ጊዜ የፌዴራል መንግስት ሠራዊትን ለማጥቃት ሞክሮ” ነበር ሲል የገለጸው መከላከያ “በአሁኑ ጊዜ የትግራይን ወርቅ እየዘረፈ በኤርትራ በኩል አድርጎ እየሸጠ ይገኛል” ብሏል።
“የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲፈርስና እንዳይሳካ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ” ይገኛል ሲል ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ የወነጀለው የመከላከያ መግለጫ “የጊዜያዊ መሥተዳድሩን ማህተም ለመንጠቅ እና በሀይል አፍርሶ ሥልጣን ለመያዝ ሞክሯል ሲል ገልጿል።
የመካላከያ ሰራዊቱ በዛሬው መግለጫው “በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሰሜን ወሎ” ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ያደራጃቸው እና የደገፋቸው ናቸው ያላቸውን ሀይሎች ደምስሻለሁ ሲል አስታውቋል።
መከላከያ በመግለጫው በፋኖ ሀይሎች ላይ “በዚህ ሁለት ቀናት ብቻ 317 የተገደለ፣ 41 የተማረከ፣ 125 የቆሰለ፣ 27እጅ የሠጠ፣ 51 በምህረት የገባ፣ 15 መረጃ አቀባይ የተያዘ፣ በድምሩ 576 የሠው ኪሳራ አድርሻለሁ ብሏል።
ማረኳቸው ካላቸው መሳሪያዎች እና ቁሳቁሶችም ውስጥ አንድ መትረየስን ጨምሮ “119 ክላሽ፣ 46 ኋላቀር መሣሪያ፣ 08 ሽጉጥ፣ 22 ቦምብ፣ 2290 የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ 28 ትጥቅ፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ተሽከርካሪ፣ ባጃጅ፣ ሞተር ሳይክል” ይገኙበታል።
“በህይወት የተረፈው” የፋኖ ሀይል “የትም የተበታተነ መሆኑ ተረጋግጧል” ሲል መከላከያ በመግለጫው አካቷል። አስ