ዜናፖለቲካ

ዜና: ጠ/ሚኒስትር አብይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ለመሾም ህዝቡ እጩዎች በኢሜይል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም፡- ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ለመሾም ህዝቡ በኢሜይል ጥቆማ እንዲሰጥ ዛሬ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በትግርኛ ባስተላለፉት መልዕክት ጠየቁ።

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትን የመሾም ስልጣን በህግ ለጠ/ሚኒስትሩ የተሰጠ ቢሆንም ህዝቡን ማሳተፍ አስፈላጊ ሀኗል ሲሉ ገልጸዋል፤ በዚህም ህዝቡ በኢሜይል ጥቆማዎቹን ይላክ ሲሉ ጠይቀዋል።

“የትግራይ ህዝብ በተሟላ መንገድ በምርጫ መሪዎቹን እስኪመርጥ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አላማዎች በብቃት ይፈጽማሉ የምትሏቸውን፣ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ይችላሉ የምትሏቸውን እጩዎች በጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኢሜይል ጥቆማችሁን ከዛሬ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አድርሱኝ” ብለዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በህገመንግስቱ፣ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እና በሚኒስትሮች ደንብ መሰረት ለሁለት አመታት በስራ ላይ መቆየቱን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ የተሰጡት አላማዎች ባለመፈጸማቸው ለተጨማሪ አንድ አመት ማራዘም አስፈላጊ ሁኖ ተገኝቷል ሲሉ ገልጸዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቋቋም ዋነኛ ግቦቹን አሳክቶ በህዝብ ለተመረጠ አስተዳደር ማስረከብ ይገባው ነበር ብለዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጡትን ቁልፍ አላማዎች በተሰጠው የጊዜ ገደብ መፈጸም አልቻለም ያሉት አብይ አህመድ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ከተሰጡት እና ካልተፈጸሙ ቁልፍ አላማዎች መካከል አንዱ ምርጫ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ምክንያት ህግ በማሻሻል የጊዜያዊ አስተዳደሩን ለአንድ አመት ማራዘም በግድ አስፈላጊ ሁኗል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አዲስ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት መሾም አስፈላጊ ሁኗል ያለው የጠ/ሚኒስትሩ መልዕክት የፌደራል መንግስት ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና የህግ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

“የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እስከ ሚቀጥለው ምርጫ ድረስ የስልጣን ግዜ እንደሚኖረው ጠ/ሚኒስትር አብይ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው ከአባላቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት መግለጻቸውን መዘገባቸን ይታወሳል።

በቀጣይ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተጨማሪ የህግ ማሻሻሎች ተደርገውበት ይመሰረታል ብለዋል። “ህግ ሲሻሻለ ደግሞ እስካሁን የነበረው አፈጻጸመ መገምገም አለበት” ሲሉ የተደመጡት ጠ/ሚኒስትሩ  “ተገምግሞ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎ የፕሪቶርያን ስምምነት በሚያከብር መንገድ  ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ስራውን እየሰራ ህዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት እና ህዝቡን የስልጣን ባለቤት የማድረጉን ሂደት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል” ሲሉ ገልጸዋል።

“ይህንን ለማድረግ ፕሬዝዳንቱ እና ምክትሎቻቸው ጋር ልዩ ልዩ ውይይቶች ስናደርግ ቆይተን፣ የተለያዩ ፕሮፖዛሎች ቀርበዋል ሲሉ ያስታወቁት ጠ/ሚኒስትሩ ከነሱ በተጨማሪ ህወሓትን ጨምሮ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

“በዚህ ንግግር አመካኝነት ህግ አሻሽለን ለሚቀጥለው አንድ አመት መጠነኛ ማሻሻያ አድርገን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይቀጥላል የሚል እምነት ነው በእኛ በኩል ያለው” ሲሉ ተደምጠዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button