
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/ 2017 ዓ/ም፦ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑበት ኩክሩክ ቀበሌ ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም በተከሰተ አዲስ ግጭት አራት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውንና ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎችና የመንግስት አካላት ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ አንድ የደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ነዋሪ፤ በዕለቱ የዳሰነች ወረዳ ወጣቶች ለቅኝት ወደ ኩርኩክ ሲጓዙ ከኬንያ ቱርካና ከመጡ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አራት ወጣቶች ሲገደሉ ሶስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብለዋል፡፡
“የእኛ ወጣቶች 11 ነበሩ፡፡ እነሱ በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ ከእነሱ ወጣቶች ጋር ተገናኝተው ተታኩሰው ከእኛ አራት ሰው ሞቷል፡፡ በኩክሩክ መስመር ነው የተከሰተው” ያሉት ነዋሪው አክለውም ከኬንያ ቱርካና አንድ ሽማግሌ በተኩስ ልውውጡ መሐል መገደላቸውን አመልክተዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ዋና የመንግሥት ተጠሪ የሆኑት አቶ መሳይ ሌበን በግጭቱ የ4 ሰዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለቅኝት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከኬንያ ቱርካና ሚሊሻዎች ጋር መጋጨታቸውን የገለጹት አቶ መሳይ አክለውም በግጭቱ ህይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ሶስት ሰዎች ቆስለው ኦምራቴ ጤና ጣቢያ ገብተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አክለውም በማግስቱ እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ከኬንያ ቱርካና የመጡ ታጣቂዎች ጎሮ በተሰኘች ስፍራ ተኩስ ከፍተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶችን ዘርፈው ለመውሰድ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም የአከባቢው ማኅበረሰብ ደርሶ ውጊያ በማካሄድ ከብቶቹን እንዳስመለሰ ተናግረው በተኩስ ልውውጡ መሀል ከኬንያ ቱርካና አንድ ሰው መገደሉን ጠቁመዋል።
አከባቢው የስጋት አከባቢ ከመሆኑ አንጻር ተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰታሉ ያሉት አቶ መሣይ የአከባቢው ማህበረሰብ የትም እንዳይሄድና ተራጋግቶ እንዲቀመጥ ከጸጥታ መዋቅራችን ጋር ሆነን እየሰራን ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑባቸው ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ከኬንያ በመጡ ታጣቂዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ ቢያንስ 13 ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ ሁለት ሰዎች በጽኑ መቁሰላቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል።
በተጨማሪም ስድስት ጀልባዎችን ጨምሮ 130 የሚደረሱ የአሣ ማጥመጃ መረቦች፣ እስከ 500 ሺህ የሚደርሱ ደረቅ አሣዎች እና በርካታ ንብረቶች” መወሰዳቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ይህን ተከትሎም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በአቶ ወገኔ ብዙነህ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ ልዑክ ከኬንያ ቱርካና ካውንቲ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጁሊያስ ካቪላ ከተመራ የካውንቲው ከፍተኛ የመንግሥት እና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች ጋር የካቲት18 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት የክልል ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በድንበር አከባቢ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታትና አከባቢውን ወደነበረበት ሠላም ለመመለስ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን የዳሰነች ወረዳ ኮሚኒኬሽን በወቅቱ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ በተከሰተ ግጭት አራት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ሶስት ሰዎች መቁሰላቸው ነው የተሰማው። አስ