
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17/ 2017 ዓ/ም፦ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑባቸው ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ከኬንያ በመጡ ታጣቂዎች በተቀሰቀሰ እና ዛሬም ድረስ በቀጠለው ግጭት ሳቢያ እስከሁን ቢያንስ 13 ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ ሁለት ሰዎች በጽኑ መቁሰላቸውን የስፍራው ነዋሪዎችና የመንግሥት አካላት ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቁ።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ስየስ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ግጭቱ ትናንት የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም መቀስቀሱን ገልጸው “ከኬንያ ቱርካና የመጡ ታጣቂዎች” በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ አስራ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
በጥቃቱ ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 2 ሰዎች በጽኑ ቆስለው በጂንካ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አያይዘውም “ስድስት ጀልባዎችን ጨምሮ 130 የሚደረሱ የአሣ ማጥመጃ መረቦች፣ እስከ 500 ሺህ የሚደርሱ ደረቅ አሣዎች እና በርካታ ንብረቶች” መወሰዳቸውን አስረድተዋል።
“ከተዘረፉት ጀልባዎች መካከል አንዱ የኔ ነው። ወደ 13 ሺህ የሚጠጉ አሳዎች ከእነ መረቡ ነው የወሰዱብኝ” ያሉት ነዋሪው አክለውም ጥቃቱ ዛሬም ድረስ ተባብሶ በመቀጠሉ በ5 ቀበሌ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አከባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ተናግረዋል።
ቶልታሌ፣ ኩክሩክ፣ ልቤሙቀት፣ ስርምሬት ኢዲቦሮን ከተባሉ ቀበሌዎች የተፈናቀሉት ነዋሪዎቹ አሁን ላይ ነበረሙስ በተባለ ስፍራ በመሄድ በሰዎች መኖሪያ ተጠልለው እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ታጣቂዎቹ በተለያዩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሲመላለሱ መመልከታቸውን የሚገልጹት እኚሁ ነዋሪ አያይዘውም በአርብቶአደሮች መካከል በሚፈጠር ግጭት መካከል “የኬንያ ጸጥታ አካላት” ጣልቃ መግባታቸውን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ዋና የመንግሥት ተጠሪ የሆኑት አቶ መሳይ ሌበን በበኩላቸው በግጭቱ የ13 ሰዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።
ግጭቱ የተቀሰቀሰው በኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ስየስ እና ስርምሬት በተሰኙ ንዑስ ቀበሌዎች መሆናቸውን የገለጹት አቶ መሣይ “ከኬንያ ሎክታንግ እና ኮክሮ አቅጣጫ የገቡ ታጣቂዎች” በአከባቢው አርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተናግረዋል።
አስቀድሞ ከኬንያ ቱርካና በመጡ የታጠቁ ሚሊሻዎች በአከባቢው አርብቶአደር ማህበረሰብ ላይ የከብት እና የንብረት ዝርፊያ ሲካሄድ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ መሳይ ይሄን አስመልክቶ ከቱርካና የክላስተር አስተባባሪዎች ጋር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት ተካሂዶ እንደነበረ ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ “ውይይቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም እና በማዘናጋት ጥቃት ከፍተውብናል” ብለዋል። በዚህም ትናንት እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ከባድ ውጊያ መደረጉን አመልክተዋል።
አያይዘውም 13 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ሁለት ሰዎች በጽኑ ቆስለው ወደ ጂንካ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እየተሰጣቸው መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም በዛሬው ዕለት “ከባድ ውጊያ በመካሄድ ላይ መሆኑን” ተናግረዋል።
“እነሱ ከእኛ ብዙ ሰው ሞቷል ነው የሚሉት ይሄ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም በእኛ በኩል። ዛሬ ደግሞ ተደራጅተው መጥተው ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ ነው። ንጹሐን አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ነው ከታጠቁት ጋር እየተፋለመ ያለው እና ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር ነው የገጠመው። እኛ ሪፖርት አርገናል ምክንያቱም እነዛ በጣም የተደራጁ ሚሊሻዎች ናቸው።” ብለዋል።
ከዚህ በፊት በአከባቢው ግጭቶች በተደጋጋሚ በአርብቶ አደሮች መካከል ሲፈጠሩ ችግሮቹን በሽምግልና የመፍታት ልምድ መኖሩን አስታውሰው “አሁን ግን በኬንያ በኩል ያሉ የመንግሥት አካላት እጃቸውን ሲያስገቡ ነገሩ እያየለ መጣ” ሲሉም አክለዋል።
“ለዚህም ታጣቂዎቹ በመንግሥታቸው በኩል ከተሽከርካሪ አንስቶ እስከ ተተኳሽ የጦር መሣሪያዎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ታዝበናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የኬንያው ዘ-ስታንዳርድ ጋዜጣ በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ዘግቧል።
በዚህም በርካታ አሳ አስጋሪዎች በቱርካና ሀይቅ ላይ ከኢትዮጵያ ሜሪሌ አከባቢ በገቡ ታጣቂዎች ስለመገደላቸው ዘገባው አካቷል።አስ