
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/ 2017 ዓ/ም፦ ጀርመን ለኢትዮጵያና ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ኤጀንሲ፣ በዩኒሴፍ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በኩል በሚተገበሩ የሰብአዊ ስራዎች ድጋፍ የሚውል ተጨማሪ 50 ሚሊዮን ዩሮ መስጠቷን አስታወቀች።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የንስ ሀነፌልድ እና የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በወቅቱ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የንስ ሀነፌልድ የአሁኑ ወቅት በዓለምአቀፍ ደረጃ ለሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴዎች ፈታኝ መሆኑን ገልጸው ሆኖም የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አክለውም የአሁኑ ድጋፍ በመጭዎቹ ዓመታት ለኢትዮጵያ የሰብአዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል። በተጨማሪም ሀገራት ዓለም አቀፉን የሰብአዊ ምላሽ ስርዓቱን ለማሻሻል አዲስ ሀሳብ ማዳበር እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ሃላፊና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጀርመን በኢትዮጵያ ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ያላትን አጋርነት አድንቀዋል።
አክለውም ጀርመን ባለፈው ዓመት የ44 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰው ከዚህም ውሶጥ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) 14.9 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ኢትዮጵያ 4.1 ሚሊዮን ዩሮ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል።
በመግለጫው ላይ ንግግር ያቀረቡት በኢትዮጵያ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተወካይ አንድሪው ምቦጎሪ በበኩላቸው ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ፍልሰተኞችን መቀበሏን አንስተዋል።
አክለውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እነዚህን ፍልሰተኞችና በአከባቢው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ የጀርመን መንግሥት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ፍልሰተኞቹ እንደ ብሔራዊ መታወቂያ ያሉ ህጋዊ ሰነዶችን እንዲያገኙና ትምህርትን የመሣሠሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችሉ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው የጀርመን ህዝብና መንግስትን ድጋፍ አመስግነው ባለፉት 4ዓመታት ጀርመን 1 ቢሊዮን ዶላር ለተ.መ.ድ የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) መስጠቷን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።አስ