ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ በዶ/ር አንዱዓለም ዳኘ ግድያ የተጠርጣረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ህክምና ክፍል ዳይሬክተር በነበሩት ዶ/ር አንዱአለም ዳኘ ግድያ የተጠርጣረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። 

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ፖሊስ ባደረገው ክትትል እሱባለው ነበረ የተባለ አንደኛውን ተጠርጣሪ ገዳይ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጸዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የጉበት፣ የቆሽት እና የሃሞት መስመር ሰብ ስፔሻሊቲ ሐኪም፣ ተመራማሪ፣ መምህር እና በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር አንዱዓለም ዳኘ ጥር 24/2017 ዓ.ም ከስራ አምሽተው ወደ ቤታቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ይታወሳል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በመግለጫው ፖሊስ ባደረገው ክትትል በቁጥጥር ስር የዋለው “ወንጀል ፈጻሚው ድርጊቱን መፈጸሙን ማመኑንም” ተናግረዋል።

“ግድያው ጥቅም ፍለጋ” የተፈጸመ መኾኑን የገለጹት ኮማንደር ዋለልኝ ግለሰቡ “ተመሳሳይ ወንጀሎችን ይፈጽም እንደነበርም” አክለው ገልጸዋል።

በግድያ ወንጀሉ ከተሳተፉት ውስጥ የተያዘው ተጠርጣሪ ዋናው መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው እርሱን ያገዙ እና ግብረ አበሮቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፖሊስ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ግድያውን ተከትሎ ጥር 29/ 2017 ዓ/ም መግለጫ ያወጣው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ዋርድ  ዶ/ር አንዱአለም ዳኘ ስም እንዲሰየምና በሆስፒታሉ ግቢ ሓውልት እንዲቆምለት መወሰኑ ይታወቃል።  

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ዩኒቨርቲው የ37 አመቱ  ዶ/ር አንዱአለም ምንም እንኳን “የተሰጠውን ጸጋ ሳይሰስት በመጠቀም ለበርካቶች የዘርፉ ባለሙያዎችና በሙያው ላገለገላቸው በርካታ ህሙማን የቅን አገልጋይነት ተምሳሌት የነበረ እንቁ ባለሙያ ነበር” ብሏል። 

አክሎም የቀረቡለትን በርካታ ዓለምአቀፍ የስራ ቅጥር ግብዣዎች ባለመቀበል ወገኑን ለማገልገል ቆርጦ የነበረ ባለሙያ ከመሆኑም በላይ በሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ክፍሉን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሻሻል እየጣረ የነበረ እና እውን ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሶ ያለፈ መሆኑንም ገልጿል።

ዶ/ር እንዱአለም በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታሪክ “የመጀመሪያውን ቀዶ ጥገና ስራ መስራቱን” የገለጸው ዩኒቨርሲቲው  እስከ ህልፈቱ ድረስ ሆስፒታሉ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበርም አስረድቷል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button