ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አከባቢዎች በተከሰተ ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ውይይት ተደረገ 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/2017 ዓ.ም፡-  ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች ወረዳ እና በሰሜን ኬንያ ቱርካና የድንበር አከባቢዎች የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በተከሰተ ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሁለቱ ወገን ልዑካን ተወያዩ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በአቶ ወገኔ ብዙነህ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ ልዑክ ከኬንያ ቱርካና ካውንቲ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጁሊያስ ካቪላ ከተመራ የካውንቲው ከፍተኛ የመንግሥት እና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች ጋር የካቲት18 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት የክልል ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በድንበር አከባቢ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታትና አከባቢውን ወደነበረበት ሠላም ለመመለስ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን የዳሰነች ወረዳ ኮሚኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ በድንበር አከባቢ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በመስራት ግጭቶችን መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል። ጠንካራ የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓትን በመዘርጋት የሚፈጠሩ ግጭቶች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ መከላከል ይቻላል ብለዋል።

የኬንያ ቱርካና ካውንቲ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጁሊያስ ካቪላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ ጠንካራ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ሆኖም በድንበር አከባቢ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የተፈጥሮ ሀብት አጠቀቀምን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።

አክለውም ችግሮችን በጋራ ትብብር በመፍታት እና በድንበር አከባቢው ዘላቂ ሠላምን በማስፈን የየሀገራቱ ዜጎች ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑባቸው ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ከኬንያ በመጡ ታጣቂዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ ቢያንስ 13 ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ ሁለት ሰዎች በጽኑ መቁሰላቸውን የስፍራው ነዋሪዎችና የመንግሥት አካላትን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በወቅቱ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ስየስ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ግጭቱ ትናንት የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም መቀስቀሱን ገልጸው “ከኬንያ ቱርካና የመጡ ታጣቂዎች” በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ አስራ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

በጥቃቱ ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 2 ሰዎች በጽኑ ቆስለው በጂንካ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የኬንያው ዘ-ስታንዳርድ ጋዜጣ በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ዘግቧል።

በዚህም በርካታ አሳ አስጋሪዎች በቱርካና ሀይቅ ላይ ከኢትዮጵያ ሜሪሌ አከባቢ በገቡ ታጣቂዎች ስለመገደላቸው ዘገባው አካቷል።

በሌላ በኩል የዳሰነች ታጣቂዎች በኬንያ ቱርካና አሳ አስጋሪዎች ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት ከጠፉ ከ20 በላይ ኬንያዊያን መካከል የኹለቱን አስከሬን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መገኘቱን የኬንያው ዘኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል

አስከሬኖቹ የተገኙት፣ የኬንያ ባለሥልጣናት በጥቃቱ ወቅት የደረሱበት ያልታወቁ ኬንያዊያን ዜጎችን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዲያፈላልጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ይሁንታ መስጠቱን ተከትሎ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button