ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት ሂጃብ ባገዱ ትምህርት ቤቶች ላይ የተመሰረተውን ክስ ውድቅ አደረገ፤ ተማሪዎችና ምክር ቤቱ ውሳኔውን አወገዙ 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/ 2017 ዓ/ም፦ የትግራይ እስላምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ በከለከሉ ትምህርት ቤቶች ላይ የተከፈተውን ክስ የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት መዝጋቱን አስታወቀ። 

ፍርድ ቤቱ ክሱን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማስተላለፍ ‘ሥልጣን እንደሌለ’ በመግለጽ ጉዳዩ ‘ሽምግልና ወይም በአስተዳደር ሂደት’ መፈታት እንዳለበት መወሰኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል።

በትግራይ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ ሀጂ መሐመድ ካህሳይ ውሳኔው የተላለፈው ቀደም ሲል በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሂጃብ መልበስ እንዳይከለከል የወሰነው ዳኛ ከኃላፊነቱ ተነስቶ በሌላ ሰው መተካቱን ተከትሎ ነው ብለዋል። “ተማሪዎች ሂጃብ እንዲለብሱ የሚፈቅድ መመሪያ ያወጣው ዳኛ በሌላ ዳኛ ተተክቷል” ሲሉ ገልጸዋል።

ሀጂ መሐመድ ሌላ ዳኛ ከተተካ በኋላ የወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለዞኑ ፍርድ ቤት እንዲያስተላልፍ ጥያቄ ቢቀርብም አዲሱ ዳኛ ፋይሉን የካቲት 20 ቀን 2017 መዝጋቱን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አክሱም ከተማ “በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሂጃብ እንዳይለብሱ” የተከለከሉ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ድርጊቱ “የትምህርት እና የሀይማኖት ነጻነታችንን ይጋፋል” ሲሉ ሲቃወሙ ቆይተዋል። ይህን ተከትሎ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ክልከላው እነዚህን መብቶች የሚፃረር ነው በማለት ወደ ፍርድ ቤት አምርቷል።

አቤቱታውን የተመለከተው የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት ቤት እንዳይገቡ የሚከለክለውን መመሪያ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ታግዶ እንዲቆይ በመወሰን መመሪያው በተማሪዎች ላይ “ሊመለስ የማይችል የመብት ጥሰት” ሊያስከትል እንደሚችል አሳስቧል

ፍርድ ቤቱ ይህን ቢወስንም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው እንዳይገቡ መከልከላቸው እንደቀጠለ ተናግረዋል። ይህም የአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከላቸውን በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የታደሙበት ሰልፍ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ ከተማ እንዲካሄድ አድርጓል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ቀጥሎም የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክለውን መመሪያ በማገድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ያልተቀበሉ የትምህርት ቤቶቹ ርዕሳነ መምህራን በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም አዟል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የፈጸሙት ድርጊት “የፍርድ ቤቱን ስልጣን የሚያዳክም ነው” በማለትም ከሷል።

ይሁን እንጂ ተማሪዎች አሁንም ትምህርታቸውን መከታተል አለመቻላቸውን እና የትግራይ ስድስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ የማህበረሰብ አባላት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን ጥሪ ቢያቀርቡም ሁኔታው አለመለወጡን ገልጸዋል።

ጉዳዩን በመከታተል ላይ ያሉት እና በመቐለ የተቃውሞ ሰልፎችን ያስተባበረው ሙባረክ በያን ክልከላውን “ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እና ህገወጥ” ሲል ገልጸውታል። “284 ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ የመልበስ መብታቸውን የሚያረጋግጡ ህጋዊ ውሳኔዎች ቢኖሩም ትምህርት ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውን” ገልጸዋል።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንድ ተማሪ በበኩሏ “ከጥቅምት ወር ጀምሮ ትምህርታችንን በትክክል መከታተል አልቻልንም። እስከ የካቲት 11 ድረስ አንዳንቅ ቀን ይፈቀድልናል አንዳንድ ቀን ደግሞ እንከለከላለን። ከዛም ከሚድ ፈተና በኋላ ሙሉ ሉሙሉ ተከለከልን።” ስትል ገልጻ፤ በርካታ ክርስቲያን ተማሪዎችና መምህራን ድጋፍ ቢሰጡንም “ጥቂት መምህራንና የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ግን እኛ ላይ ተጽዕኖ ሲያደርጉ ነበር” ብላለች።

ለብሔራዊ ፈተና እየተዘጋጀች ያለችው ሌላ ተማሪ “ወደ ትምህርት ቤት እንድንመለስ ቢፈቀድም አክሱም ውስጥ ማንም ይህን አላስከበረም” በማለት ገልጻለች። ተማሪዎቹ ሂጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት ግቢ እንዳይገቡ ስለተከለከሉ ለብሔራዊ ፈተና በሆቴሎች ውስጥ በኦንላይን መመዝገብ እንደነበረባቸውም አስረድታለች። 

ተማሪዋ አክላም እስር እና አካላዊ ጥቃትን እንደተፈጸመ ገልጻለች። ታህሳስ 5 የትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ለመግባት “የሞከሩ 20 ሴት ተማሪዎች በፖሊስ ተይዘው ሙሉ ቀኑን መታሰራቸውንና በዋስ መለቀቃቸውን” ገልጻለች። ከኪንደያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አልሙና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ቀዳማዊ ሚኒሊክ እና ከአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቁጥጥር ስር የዋሉ ተማሪዎች “በፖሊስ ጣቢያ አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል” ብላለች። 

“ከከንቲባው፣ ከትምህርት ቢሮው፣ ከጸጥታ ቢሮውና ከእስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ሞክረናል፤ መፍትሄ ግን አልተገኘም” ብላለች ተማሪዋ።

አክላም “አሁን ቤት ውስጥ ነን፣ የመማር ህገ መንግስታዊ መብታችንን ተነፍገናል” ስትል በአፅንዖት ገልጻ በመቀሌ፣ አድዋ፣ ሽሬ እና አዲግራት ጨምሮ በሌሎች የትግራይ ከተሞች የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ሂጃብ እንዲለብሱ ተፈቅዶላቸዋል ብላልች።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button