ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በአዋሽ ፈንታሌ የወጣው የሚቴን ጋዝ መጠን እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ እሳተ ገሞራ ሊያስከትል እንደሚችል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17/ 2017 ዓ/ም፦ በአዋሽ ፈንታሌ ከጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የወጣው የሚቴን ጋዝ መጠን እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ እሳተ ገሞራ ሊያስከትል እንደሚችል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነምድር መምህር  ጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) ገለጹ።

ላለፉት ሁለት ወራት በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ዙሪያ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ መሆኑን ጤናዓለም አየነው ለጋዜጣ ፕላስ ገልጸዋል። የመሬት መንቀጥቀጥ እና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተያያዙ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር ጤናዓለም፤ በኢትዮጵያ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ፍንዳታ ከመከሰቱ በፊት የሚፈጠሩ ሁኔታዎች  እየተከሰቱ ነው ብለዋል።

በአብዛኛው ሙቅ ውሃ ከመሬት አየገነፈለ የሚወጣ ሲሆን፤ አልፎ አልፎ ደግሞ አሁን በአዋሽ ፈንታሌ እንደተከሰተው የሚተኑ ጋዞች እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

በአዋሽ ፈንታሌ ከጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እየወጣ ያለው የሚቴን የጋዝ መጠን ከጊዜ ወደ ጌዜ እየጨመረ መሆኑን አመላክተዋል።

የሚቴን ጋዝ የሚከሰተው ከመሬት ውስጥ የቀለጠው አለት ከውሃ ጋር ሲገናኝ ጥልቅ ከሆነ ቦታ የኬሚካል እንቅስቃሴ/ሪአክሽን/ ሲኖር እና በሌሎች መንገዶች መሆኑን አስረድተዋል።

የሚቴን ጋዝ ከእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ጋር ተያይዞ ከሚወጡ የጋዝ አይነቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት ምምህሩ የሚቴን ጋዙ እየጨመረ መምጣት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሊያስክትል እንደሚችል አመላክተው፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በአካባቢው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የኢነርጂ ሀብት አንዱ ከመሬት ውስጥ የሚወጣ የሙቀት ሀይል ቢሆንም የሚቴን ጋዝ መውጣት ጥሩ አጋጣሚ አለመሆኑን ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሚቴን ጋዙ የአየርን የሙቀት መጠን የሚጨምር በመሆኑ በኢትዮጵያ የተከሰተው መጠኑ ከፍ እያለ ከሄደ በአካባቢ፣ በእጽዋትና እንስሳት ላይ ጉዳት ያስከትላል ሲሉ ተናግረዋል።

አካባቢን የሚበክሉ ጋዞች ሲከሰቱ በጥልቀት በመመራመር እና ሂደቱን በመከታተል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጥንቃቄ መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሚቴን ጋዙ በሂደት ወደእሳተ ገሞራ የሚቀየር ከሆነ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን ከአካባቢው የማራቅ ስራን መስራት ይገባል ብለዋል። የሚቴን ጋዙ በወጣበት አካባቢ የምርምር ማዕከል በማቋቋም የዘርፉ ባለሙያዎች ምርምር በማድረግ የሚያገኙትን ውጤት  ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሊያሳውቁ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በቅርቡ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 11:28 ላይ በኦሮሚያ ክልል መተሓራ አቅራቢያ በሬክተር ስኬል ከፍተኛ ማለትም 6.0 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ቮልካኖ ዲስከቨሪ አስታውቋል።  የመሬት መንቀጥቀጡ ማዕከል ከከተማዋ 6.5 ኪ.ሜ. ርቀት አካባቢ ላይ እንደነበር እንዲሁም ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ሪፖርቱ አመላክቷል። የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት በአካባቢው ባሉ ከተሞች መሰማቱ ተገልጿል።

በአፋር፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች ምክንያት 90,000 ሰዎች ላይ ተጽዕኖ መፈጠሩንና ሁለት ሰዎችም መጎዳታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

ባለሥልጣናት በአፋር ክልል ከ55 ሺህ በላይ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከ20ሺህ በላይ በአጠቃላይ ከ75 ሺህ በላይ ሰዎችን ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች አስወጥተዋል።

ከመስከረም ወር ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ 261 የሚሆኑ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችን መዝግቧል። የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎቹ በዋናነት የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ አካል በሆነው ፋንታሌ አካባቢ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ይህም በርካታ ቤቶች እንዲፈርሱ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button