
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሰራተኞች ከየካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የስራ አድማ በማድረግ ስራ ማቆማቸው ተገለጸ። ሰራተኞቹ የስራ አድማ ላይ የሚገኙት ይሰጣቸው የነበረ ጥቅማጥቅም፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጥ እና በቂ ደመወዝ አለማግኘታቸውነ በመግለጽ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰራተኞቹ አድማ የመጀመሪያ ቀን ቅሬታቸውን ለማቅረብ ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በማምራት ሰልፍ ማካሄዳቸው ተገልጿል። እነዚህ ያልተፈቱ ጉዳዮች በታካሚ እንክብካቤ ላይ ያደረሱትን አሉታዊ ተጽእኖ አጽንዖት ሰጥተው አስታውቀዋል።
ሰልፈኞቹ ከዩንቨርስቲው ሃላፊዎች አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጸችው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ነርስ ሪሻን ካህሳይ በዚህም ምክንያት የካቲት 14 ቀን 2017 በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሰልፋቸውን ማካሄዳቸውን አስታውቃለች።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተከስተ ብርሃን (ዶ/ር) በሆስፒታሉ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተቃውሞ ከወጡት ሰራተኞች ጋር ቢገናኙም ጉዳዩ ከዩኒቨርሲቲው አቅም በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
“የምክትል ፕሬዚዳንቱን ምላሽ ከሰማን በኋላ ትላንት የካቲት 14 ከሰዓት በኋላ ወደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በማቅናት ስለተቋረጠብን የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ላለፉት 17 ወራት ስላልተከፈለን ደመወዝ እና ስላልተሰጡን ጥቅማጥቅሞች አስመልክተን ቅሬታዎቻችንን አቅርበናል” ስትል ሪሻን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
በፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ማንም እንዳላናገራቸው የገለጸችው ሪሻን ለቀጣይ ሰኞ ጥዋት ህዳር 17 ቀን 2017 ቀጠሮ እንደተሰጣቸው አስታውቃለች።
“ከየካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት አቁሟል፣ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ እስክናገኝ ድረስ ወደ ስራችን ላለመመለስ ወስነናል” ስትል አክላለች።
ሪሻን በተጨማሪም የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ሰራተኞች በወቅቱ ሆስቲታሉ መድረስ ባለመቻላቸው ለታካሚዎች ጊዜውን የጠበቀ አገልግሎትና እንክብካቤ እንዳይሰጡ እንዳደረጋቸው አመላክታለች፤ “ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ሰራተኞቹ ቢያንስ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቀርብልን ስንጠይቅ ነበር፣ ምክንያቱም ለብዙዎቻችን በሰዓቱ ለመድረስ አማራጭ ስለሌለን ነው” ስትል ገልጻለች።
እንደ ሪሻን ገለጻ፣ በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የሆስፒታሉ ጀነሬተሮችን ማሰራት ባለመቻሉ በታካሚዎች ህይወት ላይ አስጊ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል።
የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃነ ገብረመስቀል የሆሰፒታሉ ሰራተኞች አድማ በመምታታቸው ምክንያት የድንገተኛ ህክምናን ጨምሮ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል።
በነዳጅ ዋጋ መናር ሁኔታውን ይበልጥ እንዳባባሰው የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ሰራተኞቹ የሚከፈላቸው ዝቅተኛ ክፍያ እና የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ጋር ሊጣጣም አልቻለም ሲሉ ገልጸዋል።
ብርሃኔ አክለውም ሰራተኞቹ ወደ ሆስፒታሉ በጊዜው እንዲደርሱ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲደረግላቸው እንዲሁም ለ17 ወራት ያልተከፈለ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው እየጠየቁ መሆኑ አስታውቀዋል።
“የካቲት 13 ቀን የሆስፒታሉ ሰራተኞች ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በማምራት ሰልፍ አካሂደዋል፣ በመቀጠልም በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ሰልፋቸውን ቀጥለው ‘ድምጻችን ይሰማ! ታካሚዎችን በአግባቡ ማገልገል አልቻልንም! ከባድ ችግር ገጥሞናል” የሚሉ መፎክሮችን ያሰሙ እንደነበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተከስተ ብርሃን ጉዳዩ በዋነኛነት ከበጀት እጥረት እና ከነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ብርሃነ ገብረመስቀል ገለጻ፣ ዩኒቨርሲቲው የሆስፒታሉን ፍላጎት ለማሟላት በቂ በጀት እንደሌለው አስታውቀዋል።
እስካሁንም ዩኒቨርስቲው ከሌሎች በጀቶች ያለውን ገንዘቡ ለሆስፒታሉ በመመደብ ጉዳቱን ለመቀነስ ጥረት ማድረጉን አመላክተዋል።
ጉዳዩን ዩኒቨርሲቲው ብቻውን ሊፈታ እንደማይችል ያስታወቁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አምነው ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናትን እንዲሳተፉ ለማድረገ ቃል ገብተዋል። አስ