
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት መንግስታዊ ያልሆኑ ሲቪል ተቋማት በክልሉ አክሱም ከተማ የሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ሲማሩ የቆዩ 159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች፥ በሒጃብ ምክንያት ከዘጠና አምስት ቀናት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከትምህርት ገበታ ታግደው ይገኛሉ ሲሉ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ፤ ዕልባት ይሰጠው ሲሉ ጠይቀዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና የከተማዋ ፍርድቤት ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ያሳለፉት ውሳኔዎች ሊተገበሩ ይገባል ሲሉ የሲቪክ ተቋማቱ አሳስበዋል።
በክልሉ አክሱም ከተማ የሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ሲማሩ የቆዩ 159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች፥ በሒጃብ ምክንያት ከዘጠና አምስት ቀናት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከትምህርት ገበታ ታግደው ይገኛሉ ሲሉ ሲቪል ተቋማቱ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ይኾኖ፣ ጎርዞ፣ ራይዝ ኤንድ ሻይን፣ ሕውየት፣ አምብሬላ ፎር ዘ ኒዲ እና ኖላዊ የተባሉ በሴቶች ጉዳይ ዙርያ የሚሰሩ ሲቪል ተቋማቱ እንዳሉት በአክሱም የሚገኙ ሴት ተማሪዎች ሙሉ ስሚስተር ከትምህርት ገበታ ተከልክለዋል፥ ይህ ደግሞ ማሕበራዊ እና ስነልቦናዊ ችግር በሴት ተማሪዎቹ ላይ ፈጥሯል ብለዋል።
ሲቪል ተቋማቱ “ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ በመልበሳቸው ብቻ ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ተደርጓል። ይህ ክልከላ በርካታ ጉዳቶች አስከትሎ ይገኛል። ሙሉ ስሚስተር ትምህርት አልፏቸዋል። ከጫናዎች በኋላ ለሀገራዊ ፈተና ቢመዘገቡም ወደ ትምህርት ገበታ ሊመልሷቸው አልፈቀዱም። ከዚህ በተጨማሪ ለተለያዩ ስነልቦናዊ ጫናዎች እና መነጠል ተጋልጠዋል” ብለዋል።
የሒጃብ ክልከላ ይነሳ፣ ሴት ተማሪዎቹ ከትምህርት የከለከሉ የትምህርት ቤቶች መሪዎች ተጠያቂ ይሁኑ፣ በዚህ ውዝግብ ምክንያት የጠፋው የትምህርት ግዜ መካካስ ሲሉም ስድስቱ ሲቪል ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ በአክሱም ሴት ተማሪዎች ጉዳይ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የከተማዋ ፍርድቤት ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላልፈው የነበሩ ቢሆንም፣ ይህ ውሳኔ ተግባራዊ አለመሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሲቪክ ተቋማቱም ውሳኔዎች ሊተገበሩ ይገባል ሲሉ አክለዋል።
«ሕጋዊ ውሳኔዎች ካለ የማስፈፀም ስራ በቂ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ከትምህርት ተከልክለው እያሉ ዝም ማለት አንችልም። ከተበደሉት ሴት ተማሪዎች ጎን በመቆም፥ በአስቸኳይ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ እናቀርባለን» ሲሉ ስድስቱ ሲቪክ ተቋማት መግለጻቸውን ከጀርመን ድምጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ወስዶት በአክሱም ወረዳ ፍርድቤት እየታየ የነበረ ሲሆን፥ ባለፈው የካቲት 7 ቀን ጉዳዩ ሊታይ ሲጠበቅ ዳኛ ተቀይሯል ተብሎ የቀጠሮ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን የጠቅላይ ምክርቤቱ ገልጧል።
በአክሱም ትምህርት ቤቶች የተደረገውን የሂጃብ እገዳን በመቃወም በክልሉ ዋና ከተማ በመቀለ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታደሙበት ሰልፍ መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።
ሰልፈኞቹ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲከበር መጠየቃቸውን፣ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሂጃብ ለመልበስ የሚያስችላቸውን መብት ያረጋግጣሉ የተባሉትን የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ መመሪያዎችን በመተግበር ረገድ እየታዩ ናቸው ያሏቸውን መለሳለስ በመቃወም ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ዘገባው አካቷል። አስ