ዜናፖለቲካ

ዜና: የህወሓት አመራሮች ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችላቸውን የስነምግባር መመሪያ መፈራረማቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7/2017 ዓ.ም፡- የህወሓት አመራሮች ሁሉን አቀፍ ችግሮቻቸውን በሰላምና በውይይት ለመፍታት ተስማምተዋል፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የስነ ምግባር ደንብ አውጥተው ተፈራርመዋል ሲሉ የትግራይ የሀይማኖት አባቶች ዛሬ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ ከተማ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።

የሀይማኖት አባቶቹ በመግለጫው “ስምምነቱን ወደፊት ለማራመድ በሚል ሁለቱም ወገኖች የስነ ምግባር ደንብ አውጥተው ተፈራርመዋል” ማለታቸውን ከትግራይ ቴሌቪዢን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ላለፉት ሁለት ወራት መሪዎቹ ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ለማድረግ በተናጠልም ይሁን በጋራ በተደጋጋሚ ጥረት ስናደርግ ነበር ሲሉ የገለጹት የክልሉ ምስራቃዊ ዞን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ  አቡነ መርሐ ክርስቶስ ሁሉንም ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

“የሚግባቡበት እና ወደ ሀሳብ የሚገቡበት የስነምግባር መመሪያ አዘጋጅተን ሰጠናቸው ተስማምተውበት ፈርመዋል፣ ያስኬደናል እንግባባበታለን፣ ምንም ችግር የለም ብለው አምነው ተቀብለዋል፤ ፈርመውበታል፤ እኛም አምነነበት ፈርመናል” ሲሉ በክልሉ የሚገኙ የአራቱም ሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ገልጸዋል።

የፕሪቶርየው የሰላም ስምምነት የተፈረመው ሰባት ዋነኛ ጉዳዮች ለማረጋገጥ ነው ሲል የገለጸው የሃይማኖት አባቶቹ መግለጫ እነሱም የትግራይ ህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ በህገመንግስቱ የተረጋገጠውም ትግራይ ግዛታዊ አንድነትን ለማስጠበቅ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በማድረግ እንዲቋቋሙ ማስቻል የሚሉት እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከፌደራል መንግስቱ ጋር መደበኛና ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ውይይት ለማስጀመር፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የክልሉን መልሶ ግንባታ ለመከታተል እንዲሁም ሰላማዊ እና ተአማኒነት ያለው ነጻና ፍትሃዊ ክልላዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር የሚሉት ናቸው ብለዋልል።

ይሁን እነጂ እነዚህ የፕሪቶርያው ስምምነት ዋነኛ ጉዳዮች “በትግራይ በአመራሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል ሳቢያ እንዳይሳኩ ዋነኛ እንቅፋት” መሆኑን  አስታውቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በመሆኑም አመራሮቹ ልዩነቶቻቸውን በሰላም እና በውይይት ለመፍታት ዝግጁነቶቻችንን ከማረጋገጥ ባለፈ ውይይቶቻቸው ሰላማዊ እና ህግና ስርአትን የተከተለ እንዲሆን ለማስቻል ይህንን የስነምግባር መመሪያ ለመፈራረም መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ከተስማሙባቸው የስነምግባር መመሪያዎች መካከልም “የፖለቲካ አላማዎቻችንን ለማሳካት ሀይል እንዳንጠቀም ተስማምተናል” የሚለው በመጀመሪያው አንቀጽ ተጠቅሷል፤ “አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችን ወደ አመጽ ተግባር እንዲገቡ አንገፋፋም፣ አንደግፍም፣ አንፈቅድም” የሚለውም ይገኝበታል።

ተፋራራሚዎቹ ሁለቱ ቡድኖች “ጥላቻ የሚሰብኩ እና የሚያንቋሽሽ መልዕክት ያላቸውን ንግግሮች” እንደማይጠቀሙ በስምምነታቸው ፈርመዋል፤ በአባሎቻችን እና በደጋፊዎቻችን የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮችን በፍጥነት እንኮንናለን፣  ከዚህ ተግባር እንርቃለን” ብለዋል።

ጉዳዮች ላይ እና ሃሳብ ላይ ያተኮረ ንግግር እና ፖለቲካዊ ውይይት ለማድረግ ቃል እንገባለን፣ የግለሰቦችን ክብር በሚጠብቅ መልኩ ንግግረ አናደርግም ሲሉ በስምምነቱ አመላክተዋል።

ሌላኛው የስምምነቱ መመሪያ “ማስፈራራት በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው” መሆኑን አስቀምጧል፤ “አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን በየትኛውም ሁኔታ እና ተግባር ወደ ማስፈራራት ውስጥ እንዳይገቡ ለማድረግ ሃላፊነት እንወስዳለን” ይላል።

“የቡድናችንን የበላይነት ለማሳየትም ይሁን በማናቸውም መንገድ በየትኛውም የአመጻ ተግባር ላይ አንገባም፣ አንፈቅድም” የሚለው ደግሞ ሌላኛው የስነምግባር መመሪያው አንቀጽ ሲሆን “በደጋፊዎቻችን ይህንን ስነምግባር መመሪያ የሚጥሱ ተግባራት እንዳይፈጸሙ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን” ይላል።

መረጃ አሰጣጥን እና ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ በስነምግባሩ መመሪያ ላይ የተቀመጠው አንቀጽ ሁለቱም ተፈራራሚዎች በተስማሙባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በሽማግሌዎች አማካኝነት በሚዲያ እንዲነገር እናደርጋለን የሚለው ይገኝበታል።

የስነምግባር መመሪያውን አተገባበር በተመለከተ ትክትትል የሚያደርገው አሸማጋዩ አካል እንዲሆን የተስማሙ ሲሆን “የተጣሰ መመሪያ ካለ ግልጽነት በተሞላበትና በፍጥነት ለማረም ተስማምተናል” ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ ሁሉም አካል የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። መገናኛ ብዙሃን ነገሮችን በማጋጋል ያልሆነ ቅስቀሳ ከማደረግ እንዲሁም የግለሰቦችን ስም በማጥፋት ክብር ከሚያዋርዱ ና ስም ከማጥፋት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፤ የህዝቡን አንድነት በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከወራት በፊት ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ሁለቱን የህወሓት ቡድን በማቀረራብ “ችግሮቻቸውን በመመካከር ለመፍታት ቃል እንዲገቡ ባቀረብነው ጥያቄ ላይ አዎንታዊ ምላሽ አግኝተናል” ሲሉ መግለጻቸው መዘገቡ ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button