
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17/ 2017ዓ/ም፦ በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልዑካን ቡድን የካቲት 15 ቀን በሶማሊያ ጉብኝት ማድረጉን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
ጉብኝቱ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ በቅርቡ በአዲስ አበባ ያደረጉትን የሁለትዮሽ ውይይት ተከትሎ ነው።
በጋራ መግለጫው መሠረት በሞቃዲሾ የተደረገው ውይይት “በቀጠናዊ ደህንነት” እና “በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን፣ ደህንነትን እና መረጋጋትን የማስጠበቅ” አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ ሬድዋን ሁሴን እና ሌሎች ኃላፊዎችን ያካተተ ነው። የሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ መሐመድ አሊን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ልዑካን ቡድኑን ተቀብለው በሁለቱ አገራት “ጠንካራ የሁለትዮሽ ትብብር” ጉዳይ ላይ በአጽንኦት ተወያይተዋል ተብሏል።
ይህ ስምምነት የተደረገው ባሳለፍነው አመት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የተቀሰቀሰው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መፈታቱን ተከትሎ ነው።
በወቅቱ ሶማሊያ ኢትዮጵያ “አትሚስን በሚተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም አትካተትም” ስትል በመግለጽ ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ግንኙነቷን በማጠናከር የግብፅ ወታደሮች በሶማሊያ እንዲሰፍሩና የጦር መሳሪያዎች እንዲላኩ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ በቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ታይፕ ኤርዶጋን አሸማጋይነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ውጥረቱን ለመፍታት በአንካራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነታቸው ተሻሽሏል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ታህሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርጓል። ሁለቱ አገራት ትብብርን ለማጠናከር እና ኢትዮጵያ በሶማሊያ አዲስ ተልዕኮ ተሰጥቶት በሚሰፍረው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ጦር ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ ከሶማሊያ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን በድጋሜ ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጉብኝት ተከትሎ የወጣው የጋራ በመግለጫ፤ ሁለቱም ወገኖች “የአውሶም መጀመርን እንደተቀበሉና” በቀደመው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስን) ስኬቶች ላይ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ሁለቱ አካላት በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ስራዎች ውስጥ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ሚናን አፅንዖት መስጠታቸውንና በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) የኢትዮጵያ ጦር ሃይል እንዲሰማራ መስማማታቸውን መግለጫው አስታውቋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ኃይሎች “የሃይል ሁኔታ ስምምነት” እንደሚያዘጋጁ የገለጸው መግለጫው፤ ይህም ስምምነት በታህሳስ 2023 በተፈረመው የመከላከያ ትብብር የመግባቢያ ስምምነት አካል ነው ብሏል።አስ