ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ ስምምነት ፈጸሙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3/ 2017 ዓ/ም፦ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በባሕር በር ሳቢያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ ትላንት ምሽት በቱርክ አንካራ ተስማሙ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በመካከላቸው የተፈጠረውን አልመግባባት ለመፍታት ያስችላል የተባለ ስምምነት በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አሸማጋይነት ትናንት ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ተፈራርመዋል።

የሁለቱ ሃገራት መሪዎች አንዳቸው ለሌላቸው ሉዓላዊነት እና የግዛታ አንድነት መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ለአለም አቀፍ ህግ እንዲሁም ለአፍሪካ ህብረት መርሆዎች መከበር ላይ አጽንኦት መስጠታቸው ተመላክቷል።

በዚህም የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የግዛት አንድነትን ባከበረ መልኩ ኢትዮጵያ ዘላቂ  የባሕር በር መዳረሻ እንዲኖራት ተስማምተዋል ተብሏል።

በተጨማሪም ልዩነቶችን እና አከራካሪ ጉዳዮችን ለማስወገድ እና በትብብር መንፈስ የጋራ ብልጽግናን ለመከተል ቃል ገብተዋል።

ሁለቱ ሃገራት በስምምነቱ መሰረት በአራት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ የቴክኒካል ድርድር ከጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 2025 በፊት ለመጀመር አቅደዋል።

በስምምነቱ መሰረት “ሶማሊያ በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ሰጥታለች” ተብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና እና ቀጣይነት ያለው የባህር በር መዳረሻ  እንዲኖራት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን ይህም የሊዝ ውልን ጨምሮ በኮንትራንት እና በሌሎች ሞዳሊቲዎች በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስልጣን ስር የሚተገበር መሆኑ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ውይይቱን የማቀላጠፍ ሚናቸውም እውቅና ተሰጥቶታል ተብሏል።

ሁለቱ መሪዎች ለቃል ኪዳኑ ተግባራዊ መደረግ እና ወደፊት የሚነሱ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የቱርክን ቀጣይ ድጋፍ በደስታ ተቀብለዋል።

ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ መረጋጋትን እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የባሕር በር ስምምነት ተከትሎ በቀጠናው ላይ የተፈጠረው ውጥረት ተባብሶ እንደነበረ ይታወሳል። ይህ እርምጃ በሞቃዲሾ በኩል “የሶማሊያን የግዛት ሉዓላዊነት መጣስ” ተደርጎ ተወስዷል። ይህም አለመግባባቱን የበለጠ አክካሮት ሰንብቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button